Fana: At a Speed of Life!

በፈረንጆቹ 2022 አጋማሽ በተፈጥሮ አደጋ ብቻ የ72 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ደርሷል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 2022 መጀመሪያ አጋማሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ አደጋዎች የተከሰተው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ 72 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ አንድ ዓለም አቀፍ የሕይወት እና የጤና መድን ዋስትና ድርጅት አስታወቀ፡፡

ይህን ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለው ክስተት መንስዔም ከፍተኛ መጠን ያለው ጎርፍ እና አውሎ ንፋስ እንደሆነ ነው የስዊዘርላንዱ “ስዊዝ ሪ ” የተባለ ድርጅት የገለጸው፡፡

ምንም እንኳን አሃዙ በ2021 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከተገመተው 91 ቢሊየን ዶላር ያነሰ ቢሆንም የ10 ዓመት አማካኝ ይሆናል ተብሎ ከተገመተው 74 ቢሊየን ዶላር የተጠጋጋ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ይህ ዓለም አቀፍ የመድን ዋስትና ድርጅት እንዳስታወቀው ፥ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደሆነና ለአብነት ያህልም በአውስትራሊያ እና በደቡብ አፍሪካ የተከሰቱትን ከባድ የጎርፍ አደጋዎች ጠቅሷል፡፡

በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተከሰቱት ከባድ አውሎ ነፋሶች እንዲሁ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ማድረሳቸውንም ነው ድርጅቱ የጠቆመው፡፡

በሁለተኛ የተፈጥሮ አደገኝነት ደረጃ የሚቀመጡት ጎርፍና አውሎ ንፋስ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ካሉ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች በበለጠ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነም ባለፉት አምስት ዓመታት ከተፈጠሩ ክስተቶች መገንዘብ እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

እነዚህ ተፈጥሯዊ አደጋዎች በተለይ ለአደጋው ተጋላጭ በሆኑ ስፍራዎች ተባብሰው ቀጥለዋል መባሉንም ኤ ኤፍ ፒ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.