Fana: At a Speed of Life!

በፓን አፍሪካኒዝም ላይ ያተኮረ አህጉር አቀፍ ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓን አፍሪካኒዝም ላይ ያተኮረ አህጉር አቀፍ ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ በሚካሄደው በዚህ መድረክ ከ54ቱም የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ወጣቶችና ሲቪል ማህበራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ ወጣቶች ልማትና ልህቀት ማዕከል ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

የማዕከሉ መስራችና ዳይሬክተር ጄኔራል ፉአድ ገና ጉባኤው በአፍሪካ ወጣቶች ልማትና ልህቀት ማዕከል የሚዘጋጅ ሲሆን ፥ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ፣ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች ፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ማህበረሰብ አንቂዎችና በወጣቶች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የቀደሙ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ከፍተኛ ተጋድሎ እንዳደረጉት ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ዘመናዊ ቅኝ ግዛትን በመቃወም ለአፍሪካ ጥብቅና እንዲቆም የሚያስተባብር መድረክ እንደሚሆንም ተገልጿል።

አፍሪካ ከእጅ አዙር ጫናዎች ተላቃ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄን እንድታመነጭ ጉባኤው መነሳሳት እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

የአፍሪካ ወጣቶች ልማትና ልህቀት ማዕከል መስራችና ዳይሬክተር ጄኔራል ፉአድ ገና እንደገለፁት ፥ የፊታችን ጥር 19 ለሚካሄደው ጉባኤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

በመድረኩም ፥ የኢትዮጵያዊያን የአርበኝነት ተጋድሎ ለፓን አፍሪካኒዝም እና ለአፍሪካ ነፃነት ያደረገው አስተዋፅኦ በማሳያነት ይቀርባል ተብሏል።

በሞሊቶ ኤልያስ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.