Fana: At a Speed of Life!

በ ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ የተመራ ቡድን በዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ጎበኘ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ የተመራ ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ጎበኘ፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት ከ62 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል።

በወረዳው በሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ የተመራ ቡድን በዛሬው እለት ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ሁኔታ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ የደቡብ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ጉዳዮች ሃላፊዎች፣ አርቲስቶችና የዳያስፖራ አባላት ተሳትፈዋል።

ሚኒስትሯ በጉብኝቱ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በደስታም ሆነ በችግር ወቅት የመተባበር እሴቶቻቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል ።

ከጊዜያዊ ሰብአዊ ድጋፎች ባሻገር ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባም ወይዘሮ ፊልሰን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ አርቲስቶችና የዳያስፖራ አባላትም ተፈናቃዮቹን ለመርዳት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጁን እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል።

እነሱም ህዝቡን ለማስተባበር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.