Fana: At a Speed of Life!

በ10 እና 5 ዓመቱ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከ2013 እስከ 2022 እና ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም በሚከናወኑ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ መሪ ዕቅድ ላይ የጋራ ውይይት አካሄደ፡፡

የቀረበው ዕቅድ በቀጣይ አስር ዓመታት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚያስችሉ ዋና ዋና ስራዎች እና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

የቤት ልማት አቅርቦት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ችግር በቀጣይ እንዴት ይፈታ እና ሴክተሩ የሚያቅዳቸው ዕቅዶች ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የተቃኙበትን አግባብ የተመለከቱ ሃሳብና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድም በቀረበው እቅድና በተነሱት ጥያቄዎች ላይ የማጠቃለያ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

በማጠቃለያ ሃሳበቸውም የቀረበው ዕቅድ ለቀጣይ 10 ዓመት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዋና ዋና ስራ ተጠቃሎ የቀረበበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሴክተር በፌደራል፣ በክልሎችና በከተሞች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በመተባበር እንዲተገበሩ የሚፈለጉ ግቦችን በመለየት ወደ ተጨባጭ ውጤት ለማሸጋገር በስራ ላይ የሚውል ቀጣይ አቅጣጫ ያመላከተ ነው ማለታቸውን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.