Fana: At a Speed of Life!

በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፕላንና እና ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ እና የምክር ቤቱ አባላት ተገኝተዋል።

ዶክተር ፍፁም አሰፋ የኮሚሽኑን ያለፉ አፈፃፀሞችና ተግዳሮቶች፣ የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችና የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ዕቅዱ ዝግጅቱ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ መሆኑን ያነሱ ሲሆን የሌሎች ሀገራት የረዥም ዘመን ዕቅዶቻቸው ሂደት፣ ዕቅዶችን ተግራዊ በማድረግ  የልማት ህልማቸውን እንዴት ማሳካት እንደቻሉ ልምድ በመውሰድ የዝግጅት ሂደቱን መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

ከዚሁ በመነሳት ኢትዮጵያ እየገጠማት ካለው ችግር አንጻር ለልማት ዕቅዱ ዝግጅት መነሻ የሚሆኑ በተመረጡ ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ለልማት ዕቅዱ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶች እንዲካሄዱ ተደርጎ ለዕቅድ ዝግጅቱ ግብዓት እንዲሆኑ መደረጉን አንስተዋል።

በተጨማሪ የዘላቂ ልማት ግቦችን ከአስር ዓመት የልማት ዕቅዱ ጋር ለማስተሳሰርና በወቅቱ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ የዘላቂ የልማት ግቦች ትግበራ የፋይናንስ ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ በግብዓትነት እንዲውል መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

የልማት ዕቅዱን ልዩ የሚያደርገውን ጠባይ በማንሳት የዘርፎች ትስስር ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን በማብራሪያቸው ላይ አሳይተዋል፡፡

በዚህም የዘመናዊ ግብርናን፣ የአምራች ኢንዱስትሪንና የማዕድን ዘርፎችን አንዱ ለሌላው ግብዓትና ፍላጎት በመሆን እንዲደጋገፉ፣ ንግድና የሎጅስቲክስ አገልግሎት የአምራች ዘርፎችን ትስስር በማሳለጥ፣ ምርትን ከገበያ ጋር በማገናኘት ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ፤ እንደ መንገድ ያሉ መሠረተ-ልማቶች ደግሞ ለሌሎች ዘርፎች ልማት መሠረት እንዲሆኑ እንዲሁም የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የምርታማነት ወሳኝ ማረጋገጫዎች በመሆናቸው የሁሉንም ዘርፎች ልማት በሚያሳልጡበት አግባብ መታቀዱን ዘርዝረዋል።

በእቅዱ መሠረት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ2013 እስከ 2022 ባለው ጊዜ በአማካይ 10 በመቶ ለማሳደግ ይሰራል ተብሏል፡፡

በዚሁ የልማት እቅድ በ10 ዓመት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ በ8 በመቶ እንደሚያድግ፣ በ2022 የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ 2 ሺህ 201 የአሜሪካ ዶላር ለማድረስ የታቀደ ሲሆን እንዲሁም የድህነት ምጣኔውን ከግማሽ በላይ ለመቀነስ እቅድ አለ።

በተጨማሪም ሀገራዊ የከተማ ሥራ አጥነት ምጣኔ በ2012 ከነበረበት 18 ነጥብ 7 በመቶ በ2022 ወደ 9 በመቶ ለመቀነስ እቅድ ተይዟልም ነው የተባለው፡፡

በልማት እቅዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና አገልግሎት እና ትምህርት ዋና ዋና አቅጣጫዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በጤና እቅዱ መሠረት አማካይ የመኖር እድሜ ጣሪያን በ2012 ከደረሰበት 65 ነጥብ 5 በመቶ ዓመት በ2022 ወደ 68 በመቶ ከፍ የማድረግ ግብ መጣሉን ከፕላን እና ልማት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.