Fana: At a Speed of Life!

በ10 ዓመቱ የፍትህ ዘርፍ መሪ የልማት እቅድ ወንጀልና የወንጀል ስጋትን መቀነስ፣ የሰብዓዊ መብት ማክበርና ማስከበር እና የህግ ተገዥነትን ማሳደግ ትኩረት ተደርጎባቸዋል

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 27፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) 10 ዓመት የፍትህ ዘርፍ መሪ የልማት እቅድ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና የፕላንና ልማት ኮሚሽን ባዘጋጁት ውይይት ተካሄደ።

በውይይት ላይ እቅዱ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ቀርቦ ዉይይት ተካሂዶበታል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ህጓ መሪ እቅዱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ሀገራዊ ለዉጡን ተከትሎ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

በተለይ ከዚህ ቀደም አፋኝ የነበሩ ህጎች መሻሻላቸው፣ ሰብአዊ መብቶችን ከማስከበር ረገድ የተሰጠዉ ከፍተኛ ትኩረትና የተወሰዱ የለዉጥ እርምጃዎች እና ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት የተገኙ ስኬቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

በእቅድ አፈፃፀሙ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንም የጠቀሱት ወይዘሮ አዳነች በተለይም የህግ የበላይነትንና ልማትን የሚፈታተኑ ህገወጥ ተግባራት እና ስርዓት አልበኝት መበራከት ፣ የስነ ምግባር ዝቅጠት፣ የሙስና እና የወንጀል ስጋት መጨመር፣አክራሪ ብሄርተኝነት፣ ብሄር ተኮር ግጭቶች እና ተያያዥ ተግዳሮቶች እንዲሁም ወንጀልና የወንጀል ስጋቶች መግጠማቸዉን ነው ያነሱት፡፡

በመሆኑም ተቋሙ በ2022 በፍትህ አግልግሎት የአፍሪካ ፍትህ ተቋማት ተምሳሌት ሆኖ የማየት ራእይ ላይ ለመድረስ እንደሚስራና ይህንን ራእይ ለማሳካትም የላቀ የህግ ተፈፃሚነት፣ የላቀ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ እና የተቋም ግንባታ የሚሉ ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮች ተቀርጸዉ የሚሰራ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህጓ ተናግረዋል።

እነዚህን የትኩረት መስኮች ለማሳካትም ወንጀልና የወንጀል ስጋትን መቀነስ፣ የሰብዓዊ መብት ማክበርና ማስከበር፣ የህግ ተገዥነትን ማሳደግ፣የህግ ማሻሻያ ስራዎችን ውጤታማነት ማሻሻል የሚሉና ሌሎች 10 የሚደርሱ ዋና ዋና ግቦች በመሪ እቅዱ ላይ ተካተዋል፡፡

የ10 አመት መሪ እቅዱ በዝርዝር ለዉይይት ቀርቦ ከተወያዮች አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን በቀጣይም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ምክክር እንደሚደረግበት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.