Fana: At a Speed of Life!

በ153 ሚሊየን ዶላር ወጪ ለሚገነባው የወራቤ ከተማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የቦታ መረጣ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 153 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ለሚገነባው የወራቤ ከተማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የቦታ መረጣ ተከናውኗል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ በ300 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባ ሲሆን ፥ የግንባታ ስራውን ዩ ቺን የተሰኘ የቻይና  ኩባንያ እንደሚያከናውነው የዞኑ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ገልጿል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም 20 ሺህ ለሚሆኑ የአከባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በቦታ መረጣ ስነ ስርዓቱ ወቅት የኩባንያው የስራ ሃላፊዎች ፣ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር እና ሌሎች የከተማና የዞን የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በውይይቱም ፓርኩ በጨርቃጨርቅ፣ በብረታ ብረት፣በምግብና የምግብ ውጤቶች እዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ እንደሚሰማራ የኩባንያው የስራ ሃላፊዎች ተናግረዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው፥ የፓርኩ መገንባት በወራቤ ከተማ እንዲሁም  በዞኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም  የዞኑ አስተዳደር እስከ ፕሮጀክቱ ፍፃሜ  ድርስ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፉ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።

የወራቤ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ለግንባታው ስኬት የጎላ ሚና ያላቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን  አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም ለግንባታው ስኬት የጎላ ሚና ካላቸው የመሬት አቅርቦት ጀምሮ ለውሃ ፣ መንገድ ፣ መብራትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተግባራት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ከዞኑ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.