Fana: At a Speed of Life!

በ169 ታዳጊዎች ላይ ሊፈፀም የነበረ ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በ169 ታዳጊዎች ላይ ሊፈፀም የነበረ ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ መደረጉን የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ ገለጸ፡፡

በመምሪያው የሴቶች ግንዛቤ ንቅናቄ ባለሙያ አቶ በሪሁን ታመነ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ጋብቻ ከመፈፀሙ በፊት የእድሜ እና ተያያዥ ማስረጃዎችን የሚያረጋግጡ ሶስት ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ጋብቻ ለመፈፀም የእድሜ ምርመራ ካደረጉት 585 ጥንዶች ውስጥ 169 እድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ በመሆናቸው ጋብቻቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ጋብቻ የተቋረጠባቸው ጥንዶች በስም ዝርዝር ተለይተው መያዛቸውንና በድብቅ ጋብቻ እንዳይፈፅሙ ከቀበሌ የፀጥታ አካላት እና ከትምህርት ቤቶች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ክበባት ጋር በመተባበር ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሰረት በደረሰ ጥቆማ በዝቋላ ወረዳ ያለ እድሜ ጋብቻን በድብቅ ሊፈፅሙ የነበሩ ጥንዶችን ከትምህርት ቤቶች እና ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ እንዲቋረጥ ተደርጎ ወላጆችም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።

ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፍትህ፣ ፖሊስ እና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ጥምረት ተመስርቶ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.