Fana: At a Speed of Life!

በ20/ 80 እና በ40/60 የተጀመረው የቤቶች ልማት መርሃግብር እንደሚቀጥልና አቅም ላላቸው ማህበራት ደግሞ መሬት ከሊዝ ነፃ እንደሚቀርብ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ20/ 80 እና በ40/60 የተጀመረው የቤቶች ልማት መርሃግብር እንደሚቀጥል እና አቅም ኖሮአቸው በማህበር ተደራጅተው የመገንባት ፍላጎት ላላቸው ተመዝጋቢዎች ከተማ አስተዳደሩ መሬት ከሊዝ ነፃ እንደሚያቀርብ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሀላፊ ኢንጅነር ሰናይት ዳምጠው የማህበር ቤቶች ግንባታ እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ መግለጫ ሰተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በትላንትናው እለት ባካሄደው መደበኛ ሰብሰባ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ አማራጭ የመፍትሄ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

በዚህም የ20/80 እና 40/60 መርሃግብር ተመዝጋቢ ሆነው ቤት ያልደረሳቸው ፍላጎት እና አቅም ያላቸው ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው የጋራ ቤት ለመገንባት እንዲችሉ ከሊዝ ነጻ የመሬት አቅርቦት በማድረግ እራሳቸው እንዲገነቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ለማህበር ቤት ግንባታ በ2005 ዓ.ም በ20/ 80 እና በ40/60 ፕሮግራም ለተመዘገቡ ነዋሪዎች የመገንባት ፍላጎት ላላቸው ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሲሆን ይህም የቤት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ ያቀረበው መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማህበር ቤት ልማቱ በመሀል ከተማ በተዘጋጁ ቦታዎች ግንባታቸው የሚካሄድ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ የዲዛይን እና የአስፈላጊውን የሙያ ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ሃላፊዋ ጠቁመው በ20/ 80 እና በ40/60 የተጀመረው የቤቶች ልማት መርሃግብር እንደሚቀጥል እና በ1997 ዓ.ም የተመዘገቡ ቆጣቢዎች በቅርቡ በሚወጣው ዕጣ የተካከቱ መሆኑን መግለፃቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ ነዋሪዎችም በማህበር ቤት ቢመዘገቡም እውቅና አስኪያገኙ ድረስ የጀመሩትን ቁጠባ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ሃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.