Fana: At a Speed of Life!

በ875 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል በሚቀጥለው ዓመት ስራ ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በ875 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል በሚቀጥለው ዓመት ስራ እንደሚጀምር ዬኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓለም ጸሃይ ጳውሎስ እና የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታልን የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ በ2007 ዓ.ም ተጀምሮ በ2 ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት እንደነበር የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ታሪኳ ወልደመድህን ተናግረዋል።

የወሰን ማስከበር ችግር ፣የዲዛይን መሻሻል፣የግብዓት አቅርቦት እጥረት እና ፕሮጀክቱን የተረከበው ኮንትራክተር ስራውን በተያዘለት ዕቅድ መሠረት አለማከናወን ለግንባታው መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ነው ምክትል ፕሬዚዳንቷ የገለጹት።

አሁን ላይ የሆስፒታሉ ህንጻ ግንባታ 93 ነጥብ 3 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹት ወ/ሮ ታሪኳ፣አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ ደግሞ 78 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።

በሚቀጥለው አመትም ሆስፒታሉን በከፊል ስራ ለማስጀመር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓለም ጸሃይ ጳውሎስ የሆስፒታሉን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ስራ ለማስጀመር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ የጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ወ/ሮ ዓለም ጸሃይ፤ በግንባታ ሂደቱ የተስተዋሉ ችግሮቸ መስተካከል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓለም ጸሃይ ጳውሎስ የሞሌ ሁለተኛው ትውልድ ጤና ጣቢያ የግንባታ ሂደት እና የአርባምንጭ ደም ባንክ አገልግሎት እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በመላኩ ገድፍ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.