Fana: At a Speed of Life!

“ባለሃብቶች ከልግስና ባለፈ በክልሉ ኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ሊሰማሩ ይገባል” – አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለሃብቶች ከልግስና ባለፈ በክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ሊሰማሩ ይገባል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአፋር ክልል መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከተዘጋጁ ባለሃብቶች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

አፋር ባለሃብትን ብቻ ሳይሆን ሃገርንም መጠበቅ ይችላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ባለሃብቶች የተጎዱትን ከመደገፍ ባሻገርም በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ፥ በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ በፍጥነት ለመጠገን የኢንቨስትመንት ዘርፉን መደገፍ አለበት ብሏል፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ ባለሃብቶች በሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በይፋ ስራ እንዲጀምሩ እንዲሁም በክልሉ የነበሩ ኩባንያዎችም በበለጠ አቅም መስራት የሚያስችላቸውን ውይይት አድርጓል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ በዚሁ ጊዜ በአፋር ክልል የሚያለሙ ባለሃብቶች ንብረታቸውን በሚጠብቅ እንግዳ አክባሪ ህብረተሰብ መሃል የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ለምርት ማጓጓዣነት የሚያገለግለው የጅቡቲ ወደብም ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በሃገር ውስጥ ብቻ የተመረቱ የ16 ሚሊየን ብር ምግብ እና ምግብ ነክ ድጋፍ ለክልሉ ለተፈናቀሉ ዜጎች አበርክቷል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ክልሉም ሆነ መንግሥት ብቻውን ተፈናቃዮችን መደገፍ የማይችል በመሆኑ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

“ሰብአዊነት ድንበር አይገድበውም” ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ ተጎጂዎችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ አካላትንም በክልሉ ህዝብ ስም አመስግነዋል፡፡

በአፋር ክልል 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የተጎዱ ሲሆን፥ ከ300 ሺህ በላይ ህዝብ ተፈናቅሏል፡፡

በሶዶ ለማ

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.