Fana: At a Speed of Life!

ባለፈው በጀት አመት 6 ነጥብ 1 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ተመዝግቧል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ የ6 ነጥብ 1 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት መመዝገቡን ገለጹ፡፡

5ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም ዓለም በኮሮና ቫይረስ ውስጥ በሆነበት ጊዜ ባለፈው በጀት አመት የ6 ነጥብ 1 በመቶ የምጣኔ ሀብት እድገት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

ከወቅታዊው ችግር አንጻር በበጀት አመቱ ተስፋ ሰጭ የምጣኔ ሀብት እድገት መመዝገቡን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች ለእድገቱ አይነተኛ ሚና ነበረው ብለዋል፡፡

ባለፈው በጀት አመት የኢንዱስትሪው ዘርፍ 9 በመቶ፣ አገልግሎት 5 ነጥብ 3 እንዲሁም ማዕድን ዘርፍ 91 በመቶ እድገት ተመዝግቧል ይህም ከፍተኛው ሆኗል ነው ያሉት፡፡

የጤናውና ማህበራዊ ዘርፍ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ንዑስ ዘርፍ 10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገባቸውንም አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በ2012 የበጀት ዓመት 3 ነጥብ 375 ትሪሊየን ብር ጠቅላላ ሃገራዊ ምርት መመዝገብ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

በዓመቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ለመመደብ የነበረው ጥረት የተመለሰበት እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

ሀገሪቱ የዕዳ ስረዛ እንዲደረግላት ከቡድን 20 ሀገራትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተሰራው ሥራ መልካም መሆኑንም በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ባለፈው በጀት አመት ባንኮች ተደራሽነታቸውን በማስፋት ከ1 ትሪሊየን ብር በላይ መሰብሰባቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ ውስጥም 271 ቢሊየን ብር ብድር መስጠታቸውን ጠቅሰው አብዛኛው ብድር ለግሉ ሴክተር የተሰጠ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ከአዲሱ የብር ኖት ቅያሪ ጋር ተያይዞ በርካታ አዳዲስ አካውንቶች መከፈታቸውን በማውሳትም ከዚህ ጋር ተያይዞ 37 ቢሊየን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ ባንኮች መግባቱንም ነው ያስረዱት፡፡

ላለፉት ወራት ከፍ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት አሁን ላይ በተወሰዱ እርምጃዎችና ማሻሻያዎች ቅናሽ እያሳየ መምጣቱንም ተናግረዋል፤ ግሽበቱን ለማስወገድና ለመቅረፍ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ በመጥቀስ፡፡

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ የዘንድሮው በጀት አመት በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ወሳኝ ስራዎች የሚሰሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የግድቡ ስራ እንዲደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለግድቡ ትልቅ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በመተባበር የግድቡን ስራ እንዲያሳኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንዳሉት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የፕሮጀክት ግንባታዎችን መንግስት ተገቢውን ጥናት በማድረግ በወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በመላ ሀገሪቱ ተጀምረው ያላለቁ ስታዲየሞች፣ፓርኮችና መንገዶች በርካታ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የስኳር ፕሮጀቶችን ጨምሮ ከ600 ቢሊየን ብር በላይ እዳ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ካሉባቸው ውስብስብ ችግሮች አንፃር በአጭር ጊዜ መጨረስ ፈታኝ ቢሆንም የቆሙትን ወደ ስራ በማስገባት ያልጠተናቀቁትን ለመጨረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ከትምህርት ገበታ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ 30 ሚሊየን ተማሪዎች እንዳሉና በዘንድሮው አመት ኮሮናን በመከላከል ትምህርት ማስተማር ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሮናን እየተከላከሉ ትምህርት ለማስቀጠልም ከ60 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎች መሰራታቸውን አንስተው፥ የትምህርት ሚኒስቴር ለተማሪዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች ማዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.