Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሶስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የማዕድን ምርቶች ከ178 ሚሊየን ዶላር በላይ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 3 ወራት የተለያዩ ማዕድናትን በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ178 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘቱን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
ሚኒስቴሩ በሩብ ዓመቱ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ኳርትዝ፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር፣ እምነ በረድና የመሳሰሉት ማዕድናት ወደ ውጭ በመላክ ገቢውን ማግኘቱን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስታውቀዋል፡፡
 
በባህላዊ መንገድ ከአምራቾች የቀረበ 2 ሺህ 241 ኪሎ ግራም ወርቅ ለውጭ ገበያ መቅረቡንም ጠቅሰዋል፡፡
 
ሚኒስቴሩ 750 ኪሎ ግራም ወርቅ ለመሰብሰብ አቅዶ የተደረገው የወርቅ ዋጋ ማሻሻያ ከታቀደው በ298 ነጥብ 9 በመቶ የሚልቅ ወርቅ ለውጭ ገበያ መቅረቡንም አንስተዋል፡፡
 
በባህላዊ አምራቾች የተመረተ 15 ቶን ታንታለም እንዲሁም እሴት ያልተጨመረበት 766 ነጥብ 96 ኪሎ ግራም ኦፓል ለውጭ ገበያ ቀርቧልም ነው ያሉት፡፡
 
ዕሴት የተጨመረበት 21 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም ኦፓል ለውጭ ገበያ ሲቀርብ በባህላዊ አምራቾች የተመረተ 675 ነጥብ 76 ኪሎ ግራም ኦፓል ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
 
እንዲሁም 25 ሺህ ቶን ጨው ተመርቶ ለገበያ መቅረቡንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
 
በተጨማሪም ከማዕድናት ሽያጭ ከተገኘው ገቢ ሌላ፣ ከማዕድን የሚገኝ የሮያሊቲ ገቢ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር፣ ከክልሎች ለተለያዩ አገልግሎቶች 36 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር፣ ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረቡ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ማዕድናት ሽያጭ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተነግሯል።
 
ይህ ገቢ ከፍተኛ የማዕድን ፍላጎት በመኖሩ ምክንያት ከዕቅዱ በላይ ጭማሪ የታየበት መሆኑንም በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
 
በሩብ ዓመቱ በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፉ 30 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.