Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት አምስት ወራት ያለ አግባብ የተመዘበረ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ማስመለስ ተችሏል – የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባለፉት አምስት ወራት ያለ አግባብ የተመዘበረ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉን አስታወቀ።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ እንዲሁም በጸረ ሙስና ትግሉ የተሰሩ ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ከጸረ ሙስና ትግሉ ጋር ተያይዞ ያለአግባብ በሙስና ወንጀል በተመዘበሩ ሀብቶች ላይ ምርመራ መደረጉን በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለፉት አምስት ወራት ያለ አግባብ የተመዘበረ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት ወደ መንግስት ካዝና በጥሬ ገንዘብ ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰው፥ ሌሎች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከሀገር የሚሸሹ ሀብቶችን ለማስመለስም የሀብት ማስመለስ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል ያሉት ዳይሬክተሩ ሀብቱ የሸሸባቸውን ሀገራት የመለየት ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

በዚህ ሂደትም ከሀገራቱ ጋር ውይይት ተጀምሮ ስምምነት ላይ እየተደረሰ መሆኑን አንስተው፥ በወንጀል የተገኘ ሀብት የማስመለስ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከህግ ማሻሻያ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሚወጣው አዋጅ፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ፣ እንዲሁም የፌደራል የአስተዳደር ስነ ስርአት አዋጅ በቅርቡ ጸድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይም የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሚወጣው አዋጅ ምርጫን ተከትሎ የሚኖሩ ቀውሶችን ለመከላከል እንደሚያግዝ በመታመኑ በአስቸኳይ ጸድቆ ወደ ስራ ይገባልም ነው ያሉት።

በተያያዘም ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲሁም በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ የምርመራ ሥራ መካሄዱንም አንስተዋል።

በዚህም በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ጥቅምት በወር ከተፈጠረው ድርጊት ጋር በተያያዘ እስካሁን 250 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በሰው ህይወት፣ እንዲሁም በአካል እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ከዚህ ጋር በተያያዘም ተጠርጣሪዎች ተለይተው ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አውስተዋል።

ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ የህግ የበላይነትን በማስከበሩ ሂደት ከህግ አካላት ጎን በመቆም ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.