Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሁለት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መሳብ መቻሉን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2013 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ አንኳር ተግባራትን እና የተመዘገቡ ውጤቶች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ የንግድ ከባቢን በማሻሻል፣ በኢንቨስትመንት ፍሰት፣ ከውጪ ንግድ፣ ከስራ እድል ፈጠራ ጋር የተገናኙ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ተሰርተዋል ያሏቸውን ስራዎች አንስተዋል።

የንግድ ከባቢን በማሻሻል ረገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትኩረት ሲሰራበት መቆየቱን አውስተው እነዚህ ስራዎች ኮሚሽኑ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ሲሰራ እንደነበር ነው ያነሱት።

ከእነዚህ ስራዎች ለአብነትም የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኦንላይ እንዲሆን መደረጉን ነው ያብራሩት።

ከአሰራር ማሻሻያዎች ጋር በተያያዘም የኢንቨስትመንት አዋጅን መሰረት አድርጎ ደንብ መውጣቱን እና ደንቡን መነሻ በማድረግ ባለሃብቶች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች ምላሽ የሚሰጥ ጉባኤ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ነው የገለፁት።

የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ዓለም በኮቪድ 19 እየተናወጠች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ይህን ማዕከል አድርጎ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም ለማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

በተለያዩ አገሮች በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን አቅም የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን ነው የተናገሩት።

ይህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እድል መፍጠሩን ነው ያብራሩት።

በዚህም ከሁለት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መሳብ መቻሉን ተናግረዋል።

ከመጡት ኢንቨስትመንቶች መካከል 58 በመቶ የሚሆነው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሆኑን፣አምስት በመቶ በግብርና 37 በመቶ ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ነው የገለፁት።

ኮሚሽነሯ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በዘጠኙ ወራት 70 በመቶ ክንውን ማድረስ ስለመቻሉ ነው የተናገሩት።

ፍላጎት አሳይተው ከተመለመሉ የውጭ ባለሀብቶች ወስጥ ለ132 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱንም አክለዋል።

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በተያያዘ 129 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ገልፀዋል።

ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከፓርኮች ውጪ ባሉ ኢንቨስትመንቶች ለ58ሺህ 631 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከዚህ የስራ እድል ውስጥ 85 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 237 ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ፣ ማምረት እና አግልግሎት ለማሸጋገር ስለመቻሉ በገለፃቸው ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.