Fana: At a Speed of Life!

ባንኩ በግማሽ ዓመቱ 31 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት 31 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና ከግሉ ዘርፍ 24 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

በእቅድ ተይዞ ከነበረው የ403 ቢሊየን ብር አጠቃላይ የግሉ ዘርፍ ተቀማጭ የገንዘብ ክምችትም አሁን ላይ 393 ቢሊየን ብር መድረሱንም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

ባንኩ ከሰጣቸው የተለያዩ ብድሮች 37 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 30 ቢሊየን ብር የሰበሰበ ሲሆን፥ ይህም አምና ከሰበሰበው አንፃር የ38 በመቶ እድገት ማስመዝገቡ ተገልጿል።

የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ ረገድ በግማሽ ዓመቱ ከወጪ ንግድ 139 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር፣ ከውጭ ሃዋላ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መሰብሰብ ተችሏልም ነው ያሉት።

ከብሔራዊ ባንክ የተገኘውን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉንም አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሬ ክፍያን በተመለከተ በግማሽ ዓመቱ ወደ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች፣ ለታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችና ለተለያዩ አስመጪዎች የገቢ ዕቃዎች ክፍያ ማቅረቡን ገልጸዋል።

የባንኩን አገልግሎት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በግማሽ ዓመቱ 114 አዳዲስ ቅርንጫፎችን መክፈቱንና ከእነዚህ ውስጥ 36ቱ ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ማለታቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አጠቃላይ የገንዘብ አስቀማጮች ሂሳብ ብዛት 23 ነጥብ 5 ሚሊየን መድረሱ የተገለፀ ሲሆን ከተከፈቱት አዳዲስ ሂሳቦች ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.