Fana: At a Speed of Life!

ባዕድ ነገሮችን በመቀላቀል ለገበያ በማቅረብ በተጠረጠሩ 26 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ – የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በምግብ ውስጥ ባዕድ ነገሮችን በመቀላቀል ለገበያ በማቅረብ በተጠረጠሩ 26 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት በከተማ ደረጃ ባደረጉት ቁጥጥር ነው እርምጃው የተወሰደው፡፡

እርምጃው በአዲስ ከተማ፣ በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ላይ ነው በርበሬ፣ ቅቤ እና ማር ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅለው የተገኙት ተብሏል፡፡

መሰል ህገ-ወጥ ተግባር በበዓላት ወቅት በስፋት የሚስተዋል በመሆኑ በጋራ በተደረገው ቁጥጥር ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሏል የተባለ ከ3 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ቅቤ፣ 48 ኩንታል በርበሬ፣ ከ1 ሺ ኪሎ ግራም በላይ የቅቤ መከለሻ፣ 600 ኪሎ ግራም ማር ከንግድ ተቋማቱ በኢግዚቢትነት መያዙ ነው የተገለጸው፡፡

ከባዕድ ነገሮች ጋር ተቀላቅለዋል ተብለው በኢግዚቢትነት የተያዙት ምርቶች ለናሙና ምርመራ መላካቸውም ተሰምቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ለሰው ለምግብነት የማይውል የበርበሬ ተረፈ ምርት እና የሻገተ በርበሬ መገኘቱን እና የንግድ ተቋማቱ ለምግብነት የሚውሉ ግብአቶችን የማምረት ፈቃዱ የሌላቸው እንደሆኑ በተጨማሪም ከፍተኛ የንፅህና ጉድለት ያለባቸው ሆነው መገኘታቸው የስራ ኃላፊዎቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ምርቶቹን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል በርካሽ  ለገበያ እንደሚያቀርቡ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ግዥ ሲፈፅም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክት ተላልፏል፡፡

በመጨረሻም መሰል ችግሮችን ለመጠቆም 84 82 79 የስልክ ቁጥር እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ነፃ ጥሪ መቀበያ 991ን በመጠቀም ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.