Fana: At a Speed of Life!

ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፀጥታና ደህንነት አካላት የፀረ ሽብር ሥልጠና ሰጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከአገሪቱ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ለተውጣጡ ከ330 በላይ አመራሮችና አባላት ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ።

ስልጠናው ሽብርተኝነትን መከላከልና ማክሸፍ በሚያስችሉ ስልቶች ዙሪያ እንዲሁም የሽብር ተልእኮዎችን አስቀድሞ ማወቅ የሚቻልበትን የመረጃ ሥራ በተመለከተ  የንድፈ ሃሳብና  የተግባር  መሆኑንም ኤጀንሲው አስታውቋል።

አገልግሎቱ ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለሪፐብሊካን ጋርድና ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ልዩ  ኃይል አመራሮችና አባላት ስልጠናውን የሰጠ ሲሆን፥ አላማውም እንደ አል ቃይዳ፣ አይኤስና  አልሸባብ ያሉ የሽብር ቡድኖች በኢትዮጵያና በአካባቢው አገራት ያለውን የሰላም፣ የትብብርና የልማት ማዕቀፍ ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመግታትና ለማክሸፍ መሆኑ ተገልጿል።

የሽብር ጥቃቶች ቢፈጸሙም በቀላሉና በአነስተኛ ኪሳራ ማክሸፍ የሚቻልበት ስልት ላይም የተኮረ መሆኑም  ተመልክቷል፡፡

ሥልጠናው ሽብርተኝነት የደቀነውን ስጋት፣ አሸባሪዎች በአሁኑ ወቅት የሚጠቀሙበትን  ስልት እንዲሁም የቀጣናውንና አለማቀፋዊውን ነባራዊ ሁኔታ  የዳሰሰ ሲሆን፥ ስጋቱን መመከት የሚያስችሉ  ንድፈ ሃሳባዊና ተግባራዊ የመከላከያ ዘዴዎችንም አካቷል፡፡

በእዚህም በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች  በኢትዮጵያና  በህዝቦቿ ላይ  ጉዳት ለማስከተል የሚሸርቡትን  ሴራ  ለማስቀረት  ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ተጠቅሷል። የፀጥታና የደህንነት አካላቱ ተቀያያሪ ባህሪ እያሳየ የሚገኘው ሽብርተኝነት በሚያስከትለው ጉዳት የህዝብ ሰላምና ደህንነት  እንዳይናጋ ለማድረግ ከመቼውም  ጊዜ  በላይ  ተቀናጅተውና በንቃት  እንዲሰሩም አስተዋጽኦ  እንዳለው ተገልጿል።

የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት እንዲሁም የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባና በመላ አገሪቱ በቀጣይ  ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ብሄራዊ ክብረ በዓላት  ያለምንም የፀጥታ ችግር  በሰላም  እንዲከበሩ ለማድረግ  የፀጥታና  የደህንነት  ተቋማት አስፈላጊውን  ቅድመ  ዝግጅቶች በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የብሄራዊ  መረጃና  ደህንነት  አገልግሎት በላከው መግለጫ ያመለከተ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም  ፀጥታን ሊያውኩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ሲመለከት፤ በአቅራቢያው ለሚገኙ  የፀጥታ ተቋማት  አስፈላጊውን  ጥቆማ እንዲሰጥ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.