Fana: At a Speed of Life!

ብሄራዊ መዝሙርን ጮክ ብለው የማይዘምሩ ተማሪዎችን የሚቀጣው ትምህርት ቤት

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በታይላንድ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ብሄራዊ መዝሙር በማይዘምሩ ተማሪዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ አነጋጋሪ ሆኗል።

በፓቱም ታኒ የሚገኘው ትምህርት ቤት ተማሪዎች ብሄራዊ መዝሙሩን ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው ከዘመሩ በድጋሚ እንዲዘምሩ በማድረግ ቅጣት ይጥልባቸዋል ተብሏል።

ለዚህ ደግሞ በመዝሙር ወቅት የተማሪዎቹን የድምጽ መጠን መለኪያ መሳሪያን ይጠቀማል።

በድምጽ መለኪያ መሳሪያው 85 የደረሰ የድምጽ ከፍታ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ከቅጣት ነጻ ይሆናሉ።

ይሁን እንጅ የድምጽ መጠኑ ከ80 እስከ 84 ከሆነ መዝሙሩን ሁለት ጊዜ እንደገና በቅጣት መልክ እንዲዘምሩ ይደረጋል።

በመለኪያው ከ80 ባነሰ የድምጽ መጠን የዘመሩ ተማሪዎች ደግሞ፥ መዝሙሩን በቅጣት መልክ ሶስት ጊዜ መዘመር ይኖርባቸዋል።

ትምህርት ቤቱ ይህ አሰራር በተማሪዎች ውስጥ ሥነ ምግባር እንዲሰርፅ ለማድረግ በማሰብ ነው ቢልም ከበርካቶች ተቃውሞ ገጥሞታል።

አሰራሩ ተማሪዎች ላይ ጫና የሚፈጥር እና በመስማት ችሎታቸው ላይ ተፅእኖ የሚያሳድር ነው ብለዋል አስተያየት ሰጭዎች።

ትምህርት ቤቱ ይህን ሙከራ ለሁለት ቀናት ብቻ የሞከረው ሲሆን፥ ተቃውሞውን ተከትሎ ማቋረጡን አስታውቋል።

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.