Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ወደ አንድነት እንዲመጣ ያስቻለ ፓርቲ መሆኑን በስልጠና ላይ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ከፋፋይነትና አግላይነትን በማስቀረት ወደ አንድነት እንዲመጣ ያስቻለ መሆኑን በአዳማ ከተማ ስልጠና ላይ የሚገኙ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

ከአመራሮቹ መካከል የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ አሻድሊ ሀሰን በሰጡት አስተያየት ”  ብልጽግና ፓርቲ በሀገራችን ጉዳይ ላይ እኩል እንድንወስን ያመቻቸ ነው” ብለዋል።

ፓርቲው ከፋፋይና አግላይነትን በማስቀረት ወደ አንድነት እንዲመጣ ያስቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።

“ታዳጊ ክልሎች ተብለን የተገለልን የህብረተሰብ ክፍሎች ነን፤ በመዋሃዳችን በሀገራዊ ጉዳይና የጋራ አጀንዳ ውስጥ  በእኩልነት እንድንሳተፍ ያደረገን የፖለቲካ ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል” ነው ያሉት።

ባለፉት 27 ዓመታት ሳያውቁት አስገዳጅ መመሪያዎች ከማዕከላዊ መንግስት ይሰጥ እንደነበር አቶ አሻድሊ አስታውሰዋል።

“በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  በሀገሪቱ ፖሊሲዎች፣የልማት አጀንዳዎችና የፖለቲካ አቅጣጫዎች ላይ እኩል የመወሰን እድል ያገኘንበት ነው “ብለዋል።

አጋር ድርጅቶች ተብለው ከኢህአዴግ አባላት ጋር ስልጠና እንኳን እኩል እንደማይሰጣቸው የተናገሩት አቶ አሻድሊ በአሁኑ ህብረብሔራዊ የብልጽግና ፓርቲ መብትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ይህም ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የብልጽግና ምዕራፍ ለመውሰድ ሰፊ እድል የሰጠ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው

“የፌዴራሊስት ኃይል ማለት ብልጽግና ፓርቲ ነው ” ብለዋል።

በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት ፌዴራላዊ መርሆችና ሥርዓቱን  በትክክልና ፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር ማሳያው አሁን በፓርቲው እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ምስክር እንደሆኑም አብራርተዋል።

ብልፅግና ፓርቲ ሁሉንም ያካተተና በፌዴራልዝም ሽፋን የነበረውን የፖለቲካ አሃዳዊነት የቀየረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ክልል የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ኡቻላ ቻም  ናቸው።

“በእስካሁኑ ሂደት ፓርቲው ምንም አይነት የፌዴራል ሥርዓቱንም ሆነ ህገ መንግስቱን የሚቃረን ነገር አልፈፀም ፤ የአሃዳዊነት ቅርፅ ይዞ የተፈጠረ ድርጅትም አይደለም “ብለዋል።

የራሳቸውን አክስመው  ውህድ ፓርቲ ከመሆናቸው በፊት ኢህአዴግ ራሱ ያወጣውን ያለቀላቸው አጀንዳዎች ሀሳብ እንዲሰጡበት ብቻ ይልክላቸው እንደነበርም አውስተዋል።

“ከሌሎች ክልሎች ጋር ተገናኝተን የሚንወስንበት አሰራርና ሥርዓት አልነበረም” ያሉት አቶ ኡቻላ አሁን ግን ሃሳብን ከማመንጨትና ውሳኔዎችን ከማሳለፍ ጀምሮ እየተሳተፉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የአፋር ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኤለማ አቡበከር በበኩላቸው “ወደ ብልጽግና ፓርቲ በመቀላቀላችን የተነፈገንን  በሀገር ደረጃ የመወሰን መብት አግኝተናል “ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በነበረው አግላይነት በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ወደ ኋላ መቅረታቸውንም አመልክተዋል።

“በኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ስብሳባ ላይ ክልላችንን ወክለው ያለድምፅ የሚሳተፉ ርዕሰ መስተዳደሩ ብቻ ነበሩ” ያሉት አቶ ኤለማ በአሁኑ ወቅት በእኩል ድምፅ ከክልል እስከ ዞን ያለው አመራር እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

በስልጠናው 2ሺህ የሚጠጉ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.