Fana: At a Speed of Life!

ፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ተፎካካሪ ፖርቲዎችን ማከራከር ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያዘጋጀው የመጀመሪያው የፓርቲዎች የክርክር መድረክ በፌዴራሊዝም እና ብዝሃነት ላይ በማተኮር በዛሬው እለት ተካሂዷል።

በክርክር መድረኩ ላይ የብልፅግና፣ ኢዜማ፣ ህብር ኢትዮጵያ እና መኢአድ አመራሮች የፓርቲዎቻቸውን አቋም አንፀባርቀው ነው ክርክሩን ያደረጉት።

ብልፅግና ፓርቲን በመወከል የተገኙት አቶ ፍስሃ ይታገሱ፤  ህወሃት ልዩነትን መሰረት ባደረገ ትርክት የፌዴራሊዝም ምሰሶ የሆኑትን ራስን በራስ የማስተዳደር እና ለጋራ ጉዳዮች በአብሮነት መቆምን ሲያፈራርስ መቆየቱን ተናግረዋል።

ብልፅግና ፓርቲም እነዚህን ስህተቶች አርሞ ያለፉትን ድሎች ማለትም ህዝቦች ቋንቋ እና ማንነታቸው ተከብሮ የሚኖሩበትን የፌዴራሊዝም ስርአት ይገነባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ  ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማን ወክለው የተገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ በዘር ላይ የተመሰረተው የፌዴራሊዝም ስርአት ብዝሃነትን ማስፈን አልቻልም ብለዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ “በየክልሉ የሚገኙ ዜጎችን መጤ እና ነባር እያለ  ከፍተኛ የሰው ህይወት እና የንብረት ጥፋት አስከትሏል” ይላሉ።

የፌዴራል ስርአቱ ብሄራዊ መግባባትን ከማምጣት ይልቅ ክልሎችን እርስ በርስ ለጦርነት የሚፈላለጉ አድርጓቸዋልም ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ።

ፓርቲያቸውም የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት የሚያላላ ሳይሆን የሚያጠናክርን የፌዴራሊዝም ስርአት ለመገንባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካዩ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ በኢትዮጵያ በብሄር ላይ የተንጠለጠለው የፌራሊዝም ስርአት የዜጎችን ነፃነትና እኩልነት፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሚገባው ደረጃ ማረጋገጥ አልቻለም ብለዋል።

ህብር ኢትዮጵያ የፌደራል ስርአቱ አወቃቀር ባህልን፣ የህዝብ ስነልቦና፣ ስነ ምህዳር፣ ምጣኔ ሀብት እና ሌሎችን መሰረት እንዲያደርግ በማኑፌስቶው ማስቀመጡንም ነው ያብራሩት።

መኢአድን ወክለው በክርክሩ የተሳተፉት አቶ ሰማኸኝ አብርሃም በበኩላቸው፤ የፌዴራሊዝም ስርአቱ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ባይተዋር እንዲሆኑ አድርጓል፤ በማንነታቸው ምክንያት ለተፈፀሙ ጥፋቶችም አወቃቀሩ ብሄርን መሰረት ያደረገ መሆኑ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል ነው ያሉት።

ህገመንግስቱ ተሻሽሎ የፌደራል ስርአቱ የተዋቀረበት መንገድ ካልተስተካከለ የዜጎችን መብት እና ነፃነት ማስከበርም ሆነ ራስን በራስ ማስተዳደር ማረጋገጥ አይታሰብም ባይ ናቸው።

ፓርቲዎቹ በቀጣይ ድምፅ አግኝተው መንግስት ከመሰረቱ የሚከተሉትን የፌዴራል አወቃቀር በተመለከተም ክርክር አድርገዋል።

የፌዴራል የስራ ቋንቋ እና የክልሎች ልዩ ሃይልን በተመለከተም ፓርቲዎቹ አቋማቸውን አንፀባርቀው ተከራክረዋል።

በፋሲካው ታደሰ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.