Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጀመረውን የለውጥ ሂደት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል በመሆን የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከመላው የተቋሙ አመራርና አባል ጋር በመሆን የተጀመረውን ሪፎርም አጠናክሮ ለማስቀጠልና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡
 
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተቋሙን ሲመሩት ከነበሩት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ጋር የስራ ርክክብ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡
 
በመርሃ ግብሩ ላይ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በሪፎርሙ ሂደት የጀመራቸውን ስራዎች የሚያመለክቱ ሰነዶች ርክክብ ተካሂዷል፡፡
የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተቋሙ በተካሄደው ሪፎርም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዙ መሰረቶች መጣላቸውን ገልጸዋል፡፡
 
የተጀመረውን አጠናክሮ በማስቀጠልና አዳዲስ አቅጣጫዎችን በመተለም ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ፈተና የሚያሻግር ተቋም እንደሚገነባ አረጋግጠዋል፡፡
 
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው የጸጥታ ተቋማት መጠናከር በአሁኑ ወቅት አገሪቱ እያጋጠማት ያለውን ፈተና ለመሻገር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
 
ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ተመጋጋቢ ተልዕኮ ያለው ተቋም ሲመደቡም በቆይታቸው ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ አሟጦ በመጠቀም የአገሪቱን ጸጥታና ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል፡፡
 
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቀደም ሲል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚንስትርና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤ ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.