Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የስያሜ ለውጥ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የስያሜ ለውጥ ሊያደርግ ነው።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤል፥ ስር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ላይ ያለው አገልግሎቱ የስያሜ እና አሰራር ለውጥ የሚያደርግበት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስያሜን ወደ ብሔራዊ መረጃ ማዕከል (ኤን አይ ሲ) እንዲሻሻል ይጠይቃል።

ረቂቅ አዋጁ ከፖለቲካ፣ ብሔር እና ሃይማኖት ጥገኝነት የተላቀቀ ነፃ የመረጃ እና ደህንነት ተቋም የመፍጠር የማሻሻያ ስራ አንዱ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።

ተቋማዊ ማሻሻያውን ተከትሎ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት በአስር አመት ወስጥ ሊደርስበት የሚችለውን ደረጃ የሚያመላክት የአስር አመት ስትራቴጂክ እቅድም ተዘጋጅቷል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የየወቅቱን የሀገሪቱን የሽብር ስጋት ደረጃ የሚያሳይ መዘጋጀቱም ተነግሯል።

ተቋሙ ራሱን በሰው ሃይል እና ቴክኖሎጂ ከማብቃት አንፃር በዲግሪ ደረጃ የመረጃ እና ደህንነት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

በተቋሙ ተገኝቶ የመስክ ምልከታ ያደረገው የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፥ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጠንካራ እና ዘመን ተሻጋሪ ተቋም የመፍጠር ማሻሻያውን በአግባቡ እየተገበረ ነው ብለዋል።

በዳዊት መስፍን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.