Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የሚጎለብትበትን መንገድ በጋራ መቀየስ የሚያስችል ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ ስምምነት ተፈረመ።

ማዕቀፉ ሁለት ዓመት በመውሰድ ለአየር ጠባይ ተጋላጭ በሆኑ መስኮች ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መዘጋጀቱ ተገልጿል።

ስምምነቱን ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ እና ከግብርና ሚኒስቴሮች፣ ከብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራርና ከአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽኖች ጋር ነው የተፈራረመው።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ሃይለማርያም እንደገለጹት ማዕቀፉ የአየር ጠባይና ሁኔታ ተፅዕኖ ከሚያደርስባቸው መካከል አምስቱን ዘርፎች በመምረጥ የጋራ ቡድን በማቋቋም ለሁለት ዓመታት የአየር ጠባይ አገልግሎትን ውጤታማ የሚያደርግ ሰነድ ሲዘጋጅ ቆይቷል።

ማዕቀፉ በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ መመሪያ መሰረት መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳሉትም ሚቲዎሮሎጂ ለውሃና ሀይል ልማት፣ ለግብርና፣ ለጤና፣ ለአቪዬሽን፣ ለአደጋ መከላከል፣ ለአረንጓዴ አሻራ የማይተካ ሚና ሲወጣ ቆይቷል።

ኤጀንሲው ባለፉት 40 ዓመታት በየጊዜው እያደገና እየተሻሻለ የመጣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ከኤጀንሲው በተጨማሪ የአየር ጠባይ ተፅዕኖን ለመቋቋም መረጃ ከማምረት እስከ መጠቀም ድረስ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ባለድርሻ አካላትም ሚናቸው ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት ዘርፉን ለማዘመን ተገቢውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል።

አገሪቱ በአንድ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር እየሰራች እንደምትገኝና በቀጣይ ዓመታት አስር ራዳር ለመትከል እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ስነ ምህዳርን የሚመጥኑ ጣቢያዎችን በማቋቋም መረጃ በመሰብሰብ፣ በመተንተንና በማሰራጨት ለአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግብዓት ማድረግ የኤጀንሲው ሀላፊነት ነው።

ለዚህ ይረዳው ዘንድም በዋናው መስሪያ ቤት፣ በ11 የክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላት እንዲሁም ከ 1 ሺህ በላይ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች በማቋቋም እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሰራው ስራ የአውቶማቲክ ጣቢያዎችን ቁጥር ከ20 ወደ 30 ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል።

መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር፣ የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያና ሌሎች የሚቲዎሮሎጂ ቴክኖሎጂ በማስፋፋት ከአፍሪካ የተሻለ ደረጃ ካላቸው ተቋማት አንዱ እንዲሆን እንዳስቻለውም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.