Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ ሕጋዊ ሃላፊነቱን እና ግዴታውን እንደሚወጣ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለበትን ሕጋዊ ሃላፊነት እና ግዴታ እንደሚወጣና እየተወጣም እንደሚገኝ ማረጋገጫ እንደሚሰጡ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አስታወቁ።

ሰብሳቢዋ ለፓርቲዎች አመራር አባላት፣ የፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች እና በግላቸው ለሚተሳተፉ እጩዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው “ለስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በእጩነት ስትመዘገቡ ወይም እንደ ፓርቲ እጩዎቻችሁን ስታስመዘግቡ ከፊታችን ያለው መንገድ ከፊል ተስፋ፣ ከፊል ስጋትን አዝሎ እንደሚጠብቃችሁ፣ እንደሚጠብቀን ለሁሉም ግልጽ ነገር ይመስለኛል” ብለዋል።

“ይሁንና ስጋትን ለመቀነስ ብሎም ወደ መልካም ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችለን አቅም እና እድል በየፈርጃችን ይዘን ይህን የጋራ ሙከራችንን በዝለት ሳይሆን በጥንካሬ ልንጀምረው ይገባል” ሲሉም ገልጸዋል።

አያይዘውም “በቀደሙ ምርጫዎቻችን ባልነበረ ሁኔታ የሂደቱን ዋና ተዋናዮች ማለትም ተፎካካሪዎቹን ግራ ወይም ቀኝ፣ ትንሽ ወይም ትልቅ፣ ሃገራዊ ወይስ ክልላዊ ሳይል፣ በጥረታቸው ሊያግዝ እና ሳንካቸውን ሊፈታ የተዘጋጀ፣ አቅሙን የጨመረ፣ የገለልተኝነቱን መጠን እና ስፋት ከተፅዕኖ ሁሉ የሚከላከል የምርጫ ቦርድ ሂደቱን እያስተዳደረ ይገኛልም” ነው ያሉት።

በፍትሐዊነት በተቃኘ በጎ ሐሳብ ሳይሆን በሸፍጥ፣ ሌላውን በማክበር ሳይሆን ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ በእንጻሩ የቆመውን በማጥፋት ባለመ ሐሳብ፣ የሁሉንም የዜጐችን ሐሳብን የመግለጽ ሰላማዊ ዕድል ሳይሆን ኋላቀር የሆነ ግጭታዊ መስተጋብርን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫን ያሰበ ተወዳዳሪ ቢኖር፣ ይህን ከምርጫ ፖለቲካ ውጪ የሆነ ሥራውን ለአደባባይ አውጥተው ለሰው ዓይን እና ጆሮ ሊያደርሱ የሚችሉ በቁጥር ትንሽ የማይባሉ የሚዲያ አውታሮች እንደ ሃገር ያለን መሆኑም ለተሻለ ሽግግር ወደፊት ለመቀጠል የሚያስችል አንድ በጎ እውነታ ነው በማለት ተናግረዋል።

“የሲቪል ማኅበራቶቻችንንም አናቂ ይባል ከነበረ የሕግ ማዕቀፍ ወጥተው ዜጎችን ስለ እውነተኛ ምርጫ ሊያሳውቁ እንዲሁም የምርጫ ሂደታችን ጉበኛ ሆኖ በታዛቢነት ለማገልገል በጣት በሚቆጠሩ ሳይሆን በመቶዎች በሚቆጠሩ አደረጃጀቶቻቸው ላይ መሰናዷቸውን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና እያሉ” መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአውሮፓ እና የአሜሪካ ታዛቢዎችም ይህን ለሃገራችን ትልቅ ትርጉም ያለውን ኩነት በእንግድነት ሊታዘቡ ከመንግሥት ግብዣ ደርሷቸው ከእኛ ጋር የሂደቱ አካል ሊሆኑ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነውም ብለዋል በመልዕክታቸው።

“ፓርቲዎች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢ እጩዎችን በማስመዝገብ፣ በእጩነት በመመዝገብ የምርጫ ዘመቻውን ምዕራፍ ስትከፍቱ ለሂደቱ የሚጠቅም በጎ እሴት ለመጨመር፣ በችግር ፈቺነት በጋራ ለመሥራት፣ የፖለቲካ ጥቃትን አሮጌ ባሕል ዕለት ዕለት ለመተው፣ ለዘመናዊ እና ሥልጡን ውድድር ራሳችንን ለማደስ፣ ከምንም በላይ የዜጎቻችንን ባለሥልጣንነት በማክበር” እንዲሆን ጠይቀዋል።

በዚህ አስፈላጊ እና ትልቅ ትርጉም ባለው ሥራ የሁላችንንም አብሮነት እና የእያንዳንዳችንን ድርሻ ሳንረሳ በበጎ መንፈስ የምርጫ ውድድሩን እንጀምር ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መተግበሪያን https://play.google.com/store/apps/details?id=com.companyname.FanaAm በስልክዎ በመጫን ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት፣ ኤፍኤም 98.1 እና ብሄራዊ ሬዲዮን ይከታተሉ፡፡ ቪዲዮዎችንም ይመልከቱ፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.