Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በአዋጁ አፈጻፀም ዙሪያ ምልከታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በመገኘት አዋጁን ተላልፈዋል በሚል በመጠርጠር በቁጥጥር ስር በዋሉ ሰዎች ሰብዓዊ አያያዝ ዙሪያ ምልከታ አድርጓል፡፡
 
የቦርዱ አባላት በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ በከዚራ፣ በሳቢያን እና በአዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች በመገኘት ተጠርጣሪዎች ያረፉባቸውን ቦታዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
 
ከየማረፊያ ቤቱ ከተውጣጡ የተጠርጣሪ ተወካዮች ጋር በሰብአዊ አያያዝ፣ በውሃ፣ ምግብ፣ ህክምና እና በመፀዳጃ ቤትና የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት ዙሪያም በተናጠል አወያይቷል፡፡
 
በተመሳሳይም ቦርዱ ከከተማው አስተዳደር ከንቲባ፣ ከፖሊስ ኮሚሽን፣ በየደረጃው ካሉ የስራ እና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋርም ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡
 
ከውይይቱ በኋላም ቦርዱ የከተማ አስተዳደሩ አዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ ያከናወናቸውን ጠንካራ አፈጻፀሞች እና በቀጣይ ቢታዩ ተብለው የተለዩ ነጥቦችን በሰጠው የማጠቃለያ ግብረ መልሶች አመላክቷል፡፡
 
የቦርዱ ሰብሳቢ  አቶ ለማ ተሰማ÷ የከተማ አስተዳደሩ አዋጁን ለማስፈጸም እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ጭምር ተቀናጅቶና ተናቦ መሰራት መቻሉ እና ወደስራ ከመገባቱ በፊት ለሁሉም የፀጥታ አካላት ስለአዋጁ ዓላማና አተገባበር ዙሪያ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቶ ወደስራ መገባቱን በጠንካራ አፈፃጸም መመልከቱን ተናግረዋል፡፡
 
በተጨማሪም በሰብዓዊ አያያዝ ዙሪያ ቅሬታ አለመነሳቱን፣ ተጠርጣሪዎች ምግብ፣ ውሀ፣ መጸዳጃ፣ ህክምና፣ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እንዲያገኙ፣ በቤተሰቦቻቸው እንዲጠየቁ መደረጉን ቦርዱ በጠንካራ አፈፃጸም መገምገሙን ነው የገለጹት፡፡
 
ከሌሎች ቦታዎች ለየት ባለ መልኩ በከዚራ ፖሊስ ጣቢያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ አያያዝ መከታተያ፣ መገናኛ እና ሌሎች ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል ቴክኖሎጂን በስራ ላይ ማዋል መቻሉ ተመላክቷል፡፡
 
በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በብሄር ሳይሆን ድርጊት ተኮር ላይ ብቻ መሆኑ፣ የበርካታ ተጠርጣሪዎች መዝገብ በአግባቡ ተደራጅቶ ወደክስ ሄደት ለመግባት ዝግጅት መደረጉን፣ ስጋት የማያሳድሩ፣ እድሚያቸው የገፋና ህመም ያለባቸው ተጠርጣሪዎች ተጣርቶ መለቀቅ መቻላቸው ቦርዱ በጥንካሬ ካስቀመጣቸው ውስጥ እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል፡፡
 
በሌላ በኩል በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገውን የምርመራ ሂደት በማፋጠን ጥፋተኛ የሆኑትንና ያልሆኑትን የመለየት፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣ በአንዳንድ ማረፊያ ቦታዎች ላይ የሚታየውን ጥበት ተመልክቶ የሚስተካከልበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁዋር በበኩላቸው÷ ቦርዱ የአዋጁን አፈፃጸም በተመለከተ በክልሉ ያካሄደው ምልከታ የከተማ አስተዳደሩን ይበልጥ የሚበረታታ በመሆኑ አመስግነዋል፡፡
 
ቦርዱ የሰጣቸውን ግብረ መልሶች በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች እንደመስፈንጠሪያነት እንደሚጠቀምባቸውም ነው ተናገሩት፡፡
 
የቦርዱ አባላት በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ፓሊሲ ኮሚሽን በመገኘት ኮሚሽኑ እያስገነባቸው ያሉ የቢሮ፣ የስፖርትና መዝናኛ እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ክህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.