Fana: At a Speed of Life!

ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታ ውጭ አይሆኑም- የአማራ ትምህርት ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታ ውጭ አይሆኑም ሲሉ የዐማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ ገለጹ፡፡
ህጻናት ለነገ የህይወታቸው ስንቅ የሚሆነውን ትምህርት ለመማር የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት እንዳያጋጥማቸው ለማገዝ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለባለሃብቶች፣ ለተቋማት፣ ለድርጅቶችና ግለሰቦች አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ ጥሪ አቅርቦ እንደነበረ አስታውሰዋል ኃላፊው፡፡
ጥሪውን የተቀበሉት የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ፣ አባይ ህትመት፣ የአካባቢ ደን ጥበቃ ባለስልጣን፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ እና የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ የተለያየ መጠን ያላቸው ደብተር እና እስክርቢቶ ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስረክበዋል፡፡
ድጋፉ ህጻናት በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ከትምህርት ገበታቸው ውጭ እንዳይሆኑ÷ በተባበረ ክንድ ድህነትን ማሸነፍ እንደምንችልና ወራሪው ሃይል የአማራን ህዝብና ኢትዮጵያን ማንበርከክ እንደማይችል ማሳያ ነው ብለዋል ዶክተር ማተብ፡፡
ኃላፊው ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ በትምህርት ማህበረሰቡ ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ ቢሮው በአሸባሪው የህውሓት ቡድን በደባርቅ ወረዳ ለወደሙ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የደባርቅ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት አጠቃላይ ትምህርት ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አለምነው እንደገለጹት÷ ቢሮው በዞኑ ትምህርት መምሪያ በኩል 270 ወንበሮችን ድጋፍ አድርጓል፡፡
በወረዳው በአሽባሪው የህውሓት ቡድን የ22 ትምህርት ቤቶች ቋሚ ንብረቶች፣ መጽሃፍት እና የትምህርት ማስረጃዎች መውደማቸውን ጠቁመው÷ ውድመቱ በብር ሲተመን 28 ሚሊየን 833 ሺህ 300 ብር እንደሚገመት አብራርተዋል፡፡
የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀምር መንግስትም ሆነ ባለሐብቶችና በጎ አድራጊዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.