Fana: At a Speed of Life!

ተተኳሽ ጥይቶችን  በህገ ወጥ መንገድ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ አራት  ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)  በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ5 ሺህ 500 የክላሽንኮቭ ተተኳሽ ጥይቶችን በህገ ወጥ መንገድ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ የደንበኞች ትምህርት ቡድን አስተባባሪ አቶ አሳምነው አዳነ ÷ ከማሽላ እህል  ጋር ቀላቅለው 5 ሺህ 106  ጥይቶች ይዘው የተገኙ ሁለት ግለሰቦች ከፖሊስ ጋር በመተባባር በቁጥጥር ስራ ማዋል ተችሏል።

ግለሰቦቹ  በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት በታርጋ ቁጥር ኮድ 3- 7277 አዲስ አበባ በሆነ የጭነት አይሱዙ ከቆቦ ከተማ ወደ ከሚሴ ከተማ እህል አስመስለው ጭነው ዛሬ ለማለፍ ሲሞክሩ በወልድያ ጉምሩክ መቆጣጠሪ ጣቢያ ተደርሶባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እነዚህ ግለሰቦች  አሽከርካሪውና ረዳቱ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የፌደራል፤ የክልል ፖሊስና የጉምሩክ ሰራተኞች ላደረጉት የተቀናጀ ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ህገ ወጦች የተለያየ ዘዴ ተጠቅመው ሀገርን ለማፍረስ እየሰሩ ቢሆንም በቅንጅት እየከሸፈባቸው  ነው ብለዋል፡፡

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ  ለመከላከል ህብረተሰቡም የጀመረውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡

በተመሳሳይ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በደሃና ወረዳ 456 ተተኳሽ የክላሽንኮቭ ጥይቶችን በህገ ወጥ መንገድ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አበጀ አሰፋ ÷ዛሬ በቁጥጥር ስር  ያዋሉት ግለሰቦቹ  ከሰቆጣ -ባህር ዳር ይጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተተኳሽ ጥይቱን በህገ ወጥ መንገድ ደብቀው ለማሳለፍ ሲሞክሩ ነው።

ሊደረስባቸው የተቻለውም  በወረዳው 022 ቀበሌ በሚገኘው ኬላ የፀጥታ አካላት ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ እነደሆነ አስረድተዋል።

ሁለት ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው  በምርመራ የማጣራት ስራ መጀመሩን ዋና ኢንስፔክተሩ አመልክተው ህብረተሰቡም ህገ ወጦችን  ለፀጥታ አካላት በመጠቆም  እንዲተባበር መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.