Fana: At a Speed of Life!

ተንሰራፍቶ የነበረው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በተደረገ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እየቀነሰ ነው – ጉምሩክ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቶ የነበረው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በተደረገ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እየቀነሰ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ።

የጉሙሩክ ኮሚሽን  ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ከፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በጸረ ሰላም ሃይሎች ሀገርን ለከፋ አደጋ ያጋልጡ የነበሩ  ከፍተኛ ጉዳት አድራሽ ህገወጥ መሳሪያዎች ጭምር ተግባር ላይ ውለው ጉዳት ሳይደርሱ  መያዝ መቻሉን  ገልጸዋል።

ከሃገር በላይ የራሳቸውን ኪስ በማስቀደም በህገወጥ የጦር መሳሪያ ንግዱ  የተሳተፉት ግለሰቦችም  የዚያኑ ያህል በርካቶች እንደነበሩ ነው የኮሚሽኑ መረጃ የሚያመለክተው።

በዚህ መልኩ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዝ የነበረው በምስራቅ ፣ ሰሜን ምዕራብ  እና በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በስፋት ሲከናወን የነበረው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመቀነስ ተችሏልም ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ ከተደራጀ ጀምሮ የቁጥጥር እና የክትትል የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ በተደረገ ጥብቅ ቁጥጥር  ዝውውሩን መቀነስ መቻሉን አቶ ደበሌ ቃበታ  አንስተዋል ።

የቁጥጥር ስራውም ከብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ፣ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ከመከላከያ ሰራዊት እና ከሃገር ወዳድ ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ በተደረገ የመረጃ ልውውጥ የተጠናከረ ክትትል እና ቁጥጥር ጭምር የሚሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል  ገቢና ወጪ ኮንትሮባንዱም ለበርካታ አመታት በሃገሪቱን የንግድ እቅስቃሴ ላይ አደጋ አጋልጦ ነበር ብለዋል።

ይሁንና ይህን የወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ለማዳከም የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን  ተቋማዊ አቅሙን ከማጠናከር ጀምሮ በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ምንጭን ለማድረቅ ጥናት ከማድረግ ጀምሮ ኬላዎችን በማደራጀት፣ የሰው ሃይል በማጠናከር እና የግብዓት አቅርቦት በማሟላት ደረጃ ሳይቀር ትኩረት የተሰጠባቸው ሥራዎች እየተሰሩ  መሆኑን አመላክተዋል።

በጉምሩክ በኩል የኮንትሮባንድ መተላለፊያ መንገዶችን ጠንከር አድርጎ ለመቆጣጠር በአዳዲስ መስመሮች ኬላዎች በመክፈት በአሁን ወቅት  ከ90 በላይ  ኬላዎች በስራ ላይ እንዲውሉ  መደረጉም ተገልጿል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በግማሽ አመቱ  በገቢና በወጪ ኮንትሮባንድ እና በህገ ወጥ ንግዱም ጭምር አጠቃላይ 19 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚገመቱ እቃዎችን  መያዙን ተናግረዋል።

በዚህም በተሰራ የቁጥጥር እና የከትትል ስራ በያዝነው አመት በወጪ ኮንትሮባንድ 395 ሚሊየን  ብር የሚገመቱ የወጪ ኮንትሮባንዶችን ለመያዝ ተችሏል ብለዋል።

ኮሚሽኑ አቅሙን እያጠናከረ የኮንትሮባንድ አቅስቃሴን በመግታት በዘርፉ የተሰማሩትን ህገወጦች ለህግ በማቀረብ  በርካታ ስራዎች ሰርቷል ወደፊትም ይህ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አቶ ደበሌ ገልጸዋል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.