Fana: At a Speed of Life!

ቱሪዝም ኢትዮጵያ ሃገሪቱ ካሏት የቱሪዝም መስህቦች ጋር ተመጣጣኝ ገቢ እንድታገኝ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱሪዝም ኢትዮጵያ ሀገሪቱ ካሏት የቱሪዝም መስህቦች ጋር ተመጣጣኝ ገቢ እንድታገኝ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ከፋና ብድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪዝም መስህቦች ጋር ተመጣጣኝ ገቢ እንድታገኝ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጅ በዘርፉ ያጋጠመው የገንዘብ እጥረት የማስተዋወቁን ስራ ፈታኝ እንዳደረገው አስረድተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ እንደ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ጎብኝዎችን መሳብ አለመቻሏንም እንደ ክፍተት ያነሳሉ።

የገበያ እና የማስተዋወቅ ስራ አለመስራት፣ የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ችግር፣ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት አለመስጠት፣ የመዳረሻዎች የመሰረተ ልማት ደረጃ በተገቢው ሁኔታ አለመሟላት፣ ያልተፈቱ የተቋማት ተልዕኮ እንዲሁም በየጊዜው የሚስተዋሉ የሰላም እና ደህንነት ስጋቶች ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም ለዘርፉ የተመደበው የገንዘብ መጠን ማነስ ዘርፉን ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ተናግረዋል።

ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመንቀሳቀሳቸው ከኢትዮጵያ በተሻለ ገቢ እንደሚያገኙም አንስተዋል።

አሁን ላይም ድርጅቱ የሚስተዋለውን ችግርና የቱሪዝም ፍሰቱን ለመጨመር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያን የወከሉ ሚሲዮኖች የጎብኝ ፍሰትን ለመጨመር ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም መስሪያ ቤቱ ከቱሪዝም ዘርፍ አኳያ ቻይናን እና መሰል አዳጊ የጎብኝ መነሻን ትኩረት ያደረገ እንቅስቃሴ መጀመሩም ነው የተነገረው።

በስላባት ማናዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.