Fana: At a Speed of Life!

ታላላቅ ተቋማትንና ዓለም አቀፍ አስተሳሰብን መፍጠር ሲቻል ታላቅ ሀገር ይኖራል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ታላላቅና ጽኑ ተቋማትን፣ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፍ አስተሳሰብና ባህልን መፍጠር ሲቻል ታላቅ ሀገር እንደሚኖር አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ታላቅነት የሚፈጠረው በመደመር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት ላይ ተመሥርተን ታላላቅ ሥራዎችን በጋራ መሥራት ስንችል ነው” ብለዋል።

ታላቅነት ትልቅነትን ይፈጥራል እንጂ ትልቅነት ታላቅነት አይፈጥርምም ነው ያሉት።

ግሪክና ሮም ዓለምን የቀረጹት በትልቅነታችው ሳይሆን በታላቅነታቸው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በእንግሊዝ ግዛት ፀሐይ አትጠልቅም የተባለው እንግሊዝ ትልቅ ሆና ሳይሆን በጊዜው ታላላቅ እንግሊዛውያን በአንድም በሌላም መንገድ በፈጠሩት የታላቅነት ማንነት መሆኑንም አስታውቀዋል።

ስፔንና ኦቶማን ቱርክ በአንድ ወቅት ዓለምን ያንቀጠቀጡት በትልቅነት አለመሆኑን በመጥቀስም፥ “ትልቅነት ሊያመጻድቀን ትንሽነትም ሊያሸማቅቀን አይገባም” ብለዋል በመልዕክታቸው።

“ጥረታችን በታላላቅ ኢትዮጵያውያን በኩል የኢትዮጵያን ታላቅነት መፍጠር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ታላቅነታችንን የምንፈጥረውበታላላቅ ሐሳቦች የታነጹ ታላላቅ ዜጎችንና መሪዎችን በመፍጠር” ነውም ብለዋል።

አያይዘውም ታላቅ ሀገር የሚኖረው ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ታላላቅና ጽኑ ተቋማትንና ድንበር ዘለል ዓለም አቀፍ አስተሳሰብና ባህልን መፍጠር ሲቻል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ታላቅነት የሚፈጠረው በመደመር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት ላይ በመመስረት ታላላቅ ሥራዎችን በጋራ መሥራት ሲቻል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.