Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሲቀበሉት ግብፅ ሳትቀበለው ቀርታለች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡትን ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሲቀበሉት ግብፅ ሰነዱን ሳትቀበለው ቀርታለች ።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬ የተካሄደውን የሶስትዮሽ ውይይት አስመልክቶ የውሃ ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

አዲስ አበባ (ታሕሳስ 25 ቀን 2013) የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነ መረብ ስብሰባ አካሂደዋል።

ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምከር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ነው የተካሄደው።

ሚኒስትሮቹ የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክከር ያደረጉ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ በማተኮር ምክክር ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ባለሙያዎቹ የቀረጹትን ሰነድ በበጎ እንደምትመለከተው እና በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የሱዳን ወገን በበኩሉ ሰነዱን ለሂደቱ ጠቃሚ አድርጎ እንደሚመለከተው እና በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ተጨማሪ ሚና ላይ ቢጋር በማጽደቅ ድርድሩን መቀጠል እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

የግብጽ ወገን ደግሞ ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡

የሕዳሴው ግድብ ሙሌት እና ዓመታዊ አስተዳደርን የሚመለከተው ሰነድ ላይ የሚደረገው ድርድር በአመዛኙ መግባባት የተደረሰበት ቢሆንም፣ ወደፊት በዓባይ ተፋሰስ ላይ በሚገነቡ የውሃ ልማት ሥራዎች ጋር በተያያዘ የሚኖረው ቁርኝት ዋነኛ የልዩነት ሃሳብ ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍጆታ የሌለው የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደመሆኑ በግድቡ ላይ የሚደረሰው ስምምነት ይህንኑ ከግምት ያስገባ እና የተሟላ የውሃ ስምምነት በሌለበት እና ኢፍትሃዊ አጠቃቀም በሰፈነበት ተፋሰስ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት የሚያቅብ እንዲሆን
ኢትዮጵያ አትፈቅድም።

ይህን መሰረት በማድረግም ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ እሞላል እና ዓመታዊ አስተደዳር የሚመለከተውን ደንብ በጋራ ስምምነት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ናት፡፡

በዚህ መሰረት የስምምነት አማራጮችን ለግብጽ እና ሱዳን ወገን ያቀረበች ሲሆን የሃገራቱ ምላሽ ቀና እንደሚሆን ተስፋ
ይደረጋል፡፡

በቀጣይ የሃገራቱ ባለሙያዎች በውሃ ሚኒስትሮች አመራር ስር ስብሰባቸውን በመቀጠል ስምምነት የተደረሰባቸውን እና የልዩነት ሃሳቦችን በመለየት በቀጣይ ዕሁድ ጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም ለሚካሄደው

የስድስት ሚኒስትሮች ስብሰባ ውጤቱን ያቀርባሉ፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.