Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ- ዳግማዊ አድዋ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ‘ኢትዮጵያ ውስጣዊ መዳከም አጋጥሟታል’ የሚለው የተሳሳተ ትርክት መሆኑን አንድነታችን በማጠናከርና የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ማሳየት እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

እንግሊዝ የቅኝ ግዛት አድማሷን በምስራቅ አፍሪካ ስታስፋፋ ፈረንሳይ በቅርምቱ ስትሯሯጥ ፊት ለፊት ተፋጠጡ። የዚያን ጊዜዋ እንግሊዝ ዋና የምስራቅ አፍሪካ ትኩረት የዓባይ ወንዝ ተፋሰስን መቆጣጠር ነበር።ነገርየው የውሃ ፖለቲካ ነውና ፈረንሳይም በዚህ አማተረች፤ መስፍንጠሪያዋን ደግሞ ጅቡቲ ላይ አደረገች። የፈረንሳይ መስፋፋት ለእንግሊዝ ስጋትን ደቀነ፤ እንግሊዝ የፈረንሳይ መስፋፋት ለመገደብ ጣሊያንን ወደ አካባቢው ጋበዘች ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲቲዩት ውስጥ የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ተፈሪ መኮንን የውሃውን ጂኦ ፖለቲካ እና የአድዋ ጦርነትን ያፍታቱታል ።የእንግሊዝ ሴራ ዲፕሎማሲን በመጠቀም በ1885 ጣሊያንን ወደ ምፅዋ ጋበዘች ፤ከዚያም በ1896 ወይም በእኛ አቆጣጠር በ1888 የአድዋ ጦርነት ተካሄደ። የዓባይ ውሃ ፖለቲካ ሶስቱን የአውሮፓ ሃያላንን አፋጠጠ፤ የሴራ ጂኦ ፖለቲካ ድርም በአፍሪካ ቀንድ ደራ። የአድዋ ጦርነት ዋናው ግብ ጣሊያን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝበር ነው። ለፋብሪካዎቿ ጥሬ እቃ ፍለጋ እና በቀጣናው ያላትን ተስፋፊነት እና ተሰሚነት ማጎልበቻ ነበር።

ያኔ ጀግኖች አርበኞቻችን የኢትዮጵያ የነፃነት ንስሮች ከሁሉም የሀገራችን ክፍል ነጋሪት ጎስመው ወደ አድዋ ተመሙ። የቄራስ ሃይላት በጥሬ እቃ ምዝበራ የታወሩ ግን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያን በሚገባ ያላወቁት በአድዋ ተራሮች የኢትዮጵያን ጀግኖች ጎራዴ ፉጨት መቋቋም ተሳናቸው ። ዶክተር ተፈሪ በእነዚያ የአድዋ ተራሮች የተፈጸሙ የኢትዮጵያውያንን የጦርነት ጀብዶች በስተጀርባ ያለውን ታላቅ ምስጢር ያብራራሉ። ከልዩነት ይልቅ ለሀገር ሉዓላዊነት አብሮ መሞት አብሮ ማሸነፍ!

የአድዋ ተራሮችም ለእነዚያ ቄሳር ሃይላት ተላላኪዎች የጎን ውጋት ሆኑባቸው። ምዕራባዊያን ለረዥም ዘመን የዘሩት የሀሰት ተረክ በአድዋ ባዶ ሆነ፤ ነጮች በጥቁሮች አይሸነፉም የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ልፈፋ በአድዋ ባዶ ሆነ፤ አፍሪካዊያን እና መላው የአለም ጥቁር ህዝቦች ብሎም በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩት ሌሎች ሀገራት ፓን ኢትዮጵያኒዝምን እየሰበኩ የቅኝ ግዛት ቀንበርን እስከ ወዲያኛው ጠረማመሱት፤ የጣሊያን የጥሬ እቃ እና የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራ የባህል ክለሳ በአድዋ ተደመሰሰ።

የዶክተር ጫላ ዋታ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ናቸው። አሁን ላይም በአካባቢያችን እያንዣበቡ ያሉ ሃይላት ከዚያ ዘመን ፍላጎታቸው የተለየ አይደለም ባይ ናቸው። ዶክተር ጫላ እንደሚሉት ኢትዮጵያዊያን ወቅታዊውን የምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ተገንዝበው ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም መቆም አለብን ይላሉ። የዓባይ ፖለቲካ ዛሬም ድረስ በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ተሸብቦ በአዲሱ የቅኝ ግዛት እሳቤ የተሸበቡት ፈርዖኖች ዛሬም በ1929 እና 1959 ስምምነት የመሟገቻ እና የአሳሳች ዲፕሎማሲያቸው መጋመጃ አድርገው እየባዘኑ ነው።
የግብፆች ግብ እንደ ጣሊያኖች የቅኝ ግዛት መንፈስ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝበር ነው። ዓባይ ለኢትዮጵያ ወንዝ ብቻ አይደለም በሃል፣ ፣እና አፈር ነው።ካይሮዎች ይህን በበላይነት ያለ ማንም ከልካይነት መዝረፍ ይፈልጋሉ በአርግጥ ሲዘርፉም ከርመዋል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ይህ አካሄድ በታላቁ ህዳሴ ግድብ መገታት አለበት ይላሉ። የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተናግርዋል። አሁን ላይ ግብፅም ሆነች ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉት ያለው አካሄድ ስጋት ጫሪ የሆነው ኢትዮጵያ ውስጣዊ መዳከም አጋጥሟታል ከሚል እምነት የመጣ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን አንድነታችንን በማጠናከር የተሳሳተ ትርክት መሆኑን ግድቡን በማጠናቀቅ ልናሳይ ይገባል ባይ ናቸው፤ የህዳሴ ግድብ ን በፍጥነት ማጠናቀቅ አዲሱን የግብፅ ቅኝ ግዛት መንፈስ ለዘለቄታው መስበር ነው። ጥቅሙም ለኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለም ። ለሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ጭምር እንጂ።

ለምን?

የአድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች እና አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አይቻል የሚመልሰለውን የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ ርዕዮት ዓለም ነበር ፓን ኢትዮጵያኒዝም ወደ በኋላ ላይ ፓን አፍሪካኒዝም ተሸጋገረ። አሁንም የህዳሴው ግድብ ከተጠናቀቀ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት ግብፅን እንዴት ተቋቁመን እንችላለን ለሚለው የዘመን ገርጃ መቀልበሻ ጥቁር ማቅ ማውለቂያ ማሳያ ነው። ግድቡ ለአፍሪካዊያን ሌላም የምጣኔ ሀብት ማሳያ ይዞ የሚመጣ ነው፤ እስካሁን በአፍሪካ ግዙፍ ግድቦች በራስ ሀብት ያለ ማንም የውጭ እርዳታ የተገነባ የለም፤ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ይህን የክፍለ ዘመን ግርዶሽ የሚገልጥ ነው፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአድዋ ድል ብስራት የፓን ኢትዮጵያኒዝም ርዕዮት ዓለም ግማድ ነው። ግድቡን ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ረቡ፤ ለመላው የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት እንጂ።

የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት ከግብፅ ውጭ በሄድ መለስ የፖለቲካ ውልቃት ውስጥ የሚያልፉ ናቸው። የዚህ ውልቃት ዋና ወጌሻ ደግሞ ናይልን መጠቀም እና በምጣኔ ሀብት ማደግ ነው። ግብፅ ግን ይህን ዘመን ሁሉ የእጅ አዙር እና የውክልና ጦርነት ስታካሂድበት የቀጣናውን አባል ሀገራት በጎሳ ፣በዘር እና በሃይማኖት ፣በታሪክ ተቃርኖዎች ስታባላ ከርማለች። ህዳሴ ግድብ ይህን ሁሉ አደጋ መቀልበሻ ቦይ ነው፤የታላቁ ህዳሴ ግድብ እና አድዋ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው!

የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ተፈሪ መኮንን የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት መጋመጃቸው፤ የጥላቶቻቸው መግቻ ጋሻ ነው ይላሉ። ይህ በመሆኑንም የዛሬው ትውልድ የአድዋን ድል ደማቅ በዓል አድርጎ ማክበር ያለበት ህዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ በመፍጠን እርምጃ በመራመድ መሆን ይገባዋል።

አድዋ በዓባይ ዓባይ በአድዋ የአድዋ ድል በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መደገም አለበት የሚለው ሀሳብ የሁሉም ምሁራን ምክረ ሀሳብ ነው።

በስላባት ማናዬ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.