Fana: At a Speed of Life!

ትራምፕ በአሜሪካ የደህንነት ኤጀንሲዎች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሰዋል – ጆ ባይደን

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአሜሪካ ደህንነት አስፈላጊ የሆኑ ኤጀንሲዎች በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ገለፁ።

ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ሽግግር በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት ከመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ቡድናቸው እያገኘ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይህ ንግግራቸው የተሰማው የብሄራዊ የደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪዎች ገለፃ ካደረጉላቸው በኋላ ነው ተብሏል።

ጆ ባይደን በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊነታቸው እውቅና የተሰጠው ሲሆን ከ20 ቀናት በኋላ ነጩን ቤተመንግስት ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሆኖም ተሰናበቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥቅምት ወር የተካሄደውን የምርጫ ውጤት በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርጉ ይታያል።

ከጥቅምቱ ምርጫ በኋላ ጆ ባይደን ሲደርሳቸው የነበረው ወሳኝ እና መደበኛ የፕሬዚዳንታዊ ሽግግር አካል የሆነው የደህንነት መረጃ ተቋርጦባቸው ነበር።

በትናንትናው ዕለት ጆ ባይደን ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ ተጠባባቂ የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ክርስቶፎር ሚለር ባለስልጣናት የሽግግር እንቅስቃሴውን በተቻለ ሙያዊ አቅም እየደገፉት ይገኛሉ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

የመከላከያ ሚኒስቴሩ የባይደን የሽግግር ቡድን ከጠየቀው በላይ ከ400 በላይ ባለስልጣናት ጋር ከ164 በላይ ቃለ ምልልሶችን በማድረግ 5 ሺህ ገጽ ያለው ሰነድ ማቅረቡንም ተናግረዋል።

ፔንታጎን ለጆ ባይድን የሽግግር ቡድን ሙለ በሙሉ ግልጽ መሆኑን የትራምፕ አስተዳደር ቢገልፅም ጆ ባይደን ለቡድናቸው የመከላከያ ሚኒስቴሩ፣ የማኔጅመነት ፅህፈት ቤቱ እና የበጀት ክፍሉ ግልፅ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.