Fana: At a Speed of Life!

“ትውልድ ለሰላም” የተሰኘ የሰላም ንቅናቄ መርሃ ግብር በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ትውልድ ለሰላም” የተሰኘው የሰላም የንቅናቄ መርሃ ግበር በይፋ ተጀመረ።

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተጀመረው የ“ትውልድ ለሰላም” ኢንሸቲቭ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ኢትዮጵያን ለሰላም ፊርማቸውን የሚያኖሩ ይሆናል።

የፊርማ ስነ ስርዓቱም የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በተገኙበት በዛሬው እለት በግዮን ሆቴል በይፋ ተጀምሯል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በመርሃ ግበሩ ላይ እንደተናገሩት፥ የኢትዮጵያ ችግር ድርብርብና ትናንት የፈጠረው ነው።

የፍትሕ፣ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ችግር የወለደው መሆኑን ገልጸው ለነገው ትውልድ ሁለንተናዊ ሰላም ዛሬ መስራት ይገባል ብለዋል።

ለቀጣይ ትውልድ መፃዒ ዕድል የሚውል የተስተካከለ መሰረት በመጣል በትውልድ ቅብብሎሽ ለማስቀጠል ኢንሸቲቩ የጎላ ሙና አንዳለው ገልጸዋል።

በሰላም ጉዳይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ሁሉም ዜጋ ለእንቅስቃሴው ደጋፊ በመሆን ማገዝ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።

የንቅናቄው አስተባባሪ ወጣት ሳሮን ተስፋወርቅ ዓላማው፥ አገራዊ የጋራ ችግሮችን በጋራ መፍትሔ በማምጣት ሰላም ለማስፈን የሰላም ፍኖተ ካርታ ተቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፃለች።

በሂደቱ የሰላም ፕሮግራሞች ተቀርፀው በህዝብ መካከል መተማመን ለመፍጠር፣ ልዩነቶችን በሰላም ለመፍታትና የሻከሩ ግንኙነቶችን ለማሻሻል መስራት ይሆናል።

ለግጭት መንስኤዎችና መፍትሔዎች የሚሆኑ የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎችም እንደሚኖሩ ጠቁማለች።

የጥናት ውጤቶችም ለፓለቲካ ልሂቃን፣ ለህዝብና ለመንግሥት ቀርበው ምክክር የሚደረግባቸው መሆኑን ገልጻለች።

ኢኒሼቲቩ ከማንኛውም ሃይማኖት፣ ብሔርና የፓለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ለኢትዮጵያ የጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማምጣት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጣለች።

ከሀይማኖት፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ሲቪክ ማህበራት ጋር በጋራ ይሰራል ተብሏል።

ከሌሎች ከሰላም ጉዳይ ከሚሰሩ አካላት የሚለየው ሰላም ጉዳይ ከመንግሥት ወደ ታች የሚወርድ ሳይሆን ከሰላም ባለቤቱ ህዝብ ወደ ላይ የሚሄድ የሰላም ፕሮግራም መሆኑ እንደሆነ ገልፀዋል።

ፊርማው ለቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሚቀጥል ሲሆን ኢንሸቲቩ /ፕሮግራሙ/ ደግሞ ለቀጣይ ዘጠኝ ወራት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚካሄድ ይሆናል።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገውን ኢንሸቲቭ ወደ ስራ ለመግማባት ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥናት ሲካሄድ መቆየቱንም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.