Fana: At a Speed of Life!

ቻርልስ ንዴማ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት አውድ ለተፈፀሙ ከባድ ጥሰቶች ባህሪ የሚመጥን መፍትሄ ለማቅረብ እየተካሄደ ያለውን ምርመራ አደነቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሀገራዊ ፅህፈት ቤት ምክትል ተጠሪ ቻርለስ ንዴማ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት አውድ ለተፈፀሙ ከባድ ጥሰቶች ባህሪ የሚመጥን መፍትሄ ለማቅረብ እየተካሄደ ያለው ጥልቅ ምርመራና አገር እንዲማርበት እየተሰራ ያለውን ሁሉን አቀፍ ሂደት አደነቁ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት አውድ ጾታን መሰረት አድርገው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ለማጣራት ለተሰማራው ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ ቡድን ዓለም አቀፋዊ ደረጃን መሰረት ያደረገ ስልጠና ከተለያዩ የተመድ አጋር ባለድርሻ አገራትና ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰጠ ነው፡፡

ስልጠናው በዋናነት የወንጀል ተጠያቂነትን ለመመስረት በሚያስችሉ የአገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ህግ ማዕቀፎች ጥሰቶች ሲከሰቱ ምርመራ በሚካሄድባቸው ቴክኒካዊ ስልቶች እንዲሁም ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ሰለባዎች እና ምስክሮች የህግ፣ የስነ-ልቦና፣ የህክምና እና ቁሳቁስ ድጋፎችን ከማህበረሰቡና መንግስት የሚያገኙበትን አሰራር ምንነት እንደሚሸፍን ተገልጿል።

የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ፥ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ፣ ጾታዊ ጥቃቶችን የማስቆም፣ ሲፈጸሙም መርምሮ የማስቀጣት ሃላፊነት በቀዳሚነት የመንግስት ሃላፊነት በመሆኑ ሁላችንም ለተጠቁ ሰዎች ፍትህን ለመስጠት በተለየ ሁኔታ መንቀሳቀስና ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት መስራት ይገባል ብለዋል።

በተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሀገራዊ ፅህፈት ቤት ምክትል ተጠሪ ቻርለስ ንዴማ በበኩላቸው፥ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት አውድ ለተፈፀሙ ከባድ ጥሰቶች ባህሪ የሚመጥን መፍትሄን ከማቅረብ አንፃር እስካሁን እየተካሄደ ያለው ጥልቅ ምርመራና አገር እንዲማርበት እየተሰራ ያለውን ሁሉን አቀፍ ሂደት አድንቀዋል።

አያይዘውም ምርመራዎች በፍጥነት ተጠናቀው ክስ መመስረት መጀመር እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተመድ የሴቶች የኢትዮጵያ ተወካይ አና ሙታቫቲ ፥ ተቋሙ የሴቶችን ጥቃት ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት አንጻር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኦሞድ ፥ ተቋማቸው የሚመራውና በሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ስር ከተቋቋሙት አራት አበይት ኮሚቴዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ኮሚቴ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና ለመደገፍ ተጨባጭ እቅዶችን አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለታቸውን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.