Fana: At a Speed of Life!

ቻይና በዓለም ቀዳሚ ያደረጋትን የሞባይል ብሮድባንድ እና የፋይበር ኦፕቲክ አገልግሎት ገነባች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በዓለም ቀዳሚ ያደረጋትን የሞባይል ብሮድባንድ እና የፋይበር ኦፕቲክ አገልግሎት መገንባቷን የ”ዓለም የቴሌኮሙኒኬሽን እና የመረጃ ማኅበረሰብ ቀን” ባከበረችበት ወቅት ይፋ አደረገች፡፡

የቻይና የኢንዱስትሪ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምክትል ሚኒስትር ዣንግ ያንሚንግ እንደገለጹት ÷ የሀገሪቷ የመሥመር ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ከ100 ሜጋ ባይት በሰከንድ ወደ 1 ሺህ ሜጋ ባይት በሰከንድ አድጓል፡፡

በፈረንጆቹ 2012 በቻይና የኦፕቲካል ፋይበር ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ ደንበኞች ቁጥር በመቶኛ ከ10 በመቶ በታች የነበረ ሲሆን በ2021 የተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 94 ነጥብ 3 በመቶ አድጓል፡፡

በተጨማሪም ቻይና 1 ነጥብ 6 ሚሊየን የአምሥተኛው ትውልድ (5ጂ) የኢንተርኔት ማዕከላትን በሀገሪቷ ክፍሎች ሁሉ ገንብታለች፡፡

ይህም የዓለምን የአምሥተኛው ትውልድ የኢንተርኔት ኔትወርክ አገልግሎት ማዕከላት 60 በመቶውን እንደሚሸፍን ነው ሲ ጂ ቲ ኤን የዘገበው፡፡

በአሁኑ ወቅት በቻይና መንግስት ድጋፍ 130 ሺህ መንደሮች የፋይበር ኦፕቲክ ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆኑ በ60 ሺህ መንደሮችም የአራተኛው ትውልድ (4 ጂ) የኢንተርኔት ማዕከላት ተገንብተዋል፡፡

ከ70 በመቶ በታች የነበረው የሀገሪቷ ገጠር አካባቢዎች የብሮድባንድ አገልግሎት ሽፋንም አድጎ አካባቢዎቹ በሙሉ ብሮድባንድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ዣንግ ጠቁመዋል፡፡

ቻይና የአምሥተኛው ትውልድ (5 ጂ) የኢንተርኔት አገልግሎት በትራንስፖርት፣ በሕክምና፣ በትምህርት፣ በባሕልና ቱሪዝም ፣ በኢንዱስትሪ እንዲሁም በሀገሪቷ የግብይት አገልግሎት ዘርፎች ላይ በመጠቀም የመረጃ አገልግሎት ፍጥነት እና ዝመና እያሳለጠች ነው ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.