Fana: At a Speed of Life!

ቻይና የናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እንደመግባት ይቆጠራል አለች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን የሚያደርጉት ጉዞ በቻይና የውስጥ ጉዳይ እንደመግባት እንደምትቆጥር ቤጂንግ ገለፀች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ አፈ-ጉባዔዋ ጉብኝታቸውን እንዲተዉ በተደጋጋሚ ለአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን በሥልክ መንገራቸውንም አስታውሷል።

የአፈጉባኤዋ ጉብኝት ማድረግ የቻይናን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መድፈር መሆኑን እንዲሁም የአንዲት ቻይና ፖሊስን የሚፃረር መሆኑን አስረግጧል መግለጫው።

ይህ ሁሉ ሲሆን የቻይና ጦር ቁጭ ብሎ እንደማይመለከት በመጠቆምም፥ ሁኔታው የታይዋን ሰርጥን ወደ አለመረጋጋት እንደሚከት አስጠንቅቋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ዣንግ ጃን በበኩላቸው፥ ፔሎሲ በታይዋን አደርጋለሁ የሚሉት ጉብኝት ቻይና “ሊጣስ የማይችል” ብላ ያሰመረችውን የአንድነት መርህ ቀይ መስመር የሚጥስ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ሊያስቡበት ይገባል ብለዋል፡፡

ታይዋን በምንም መልኩ ለድርድር የማትቀርብ የቻይና ግዛት አካል መሆኗንም ነው ያሰመሩበት፡፡

የቻይና መንግስት እና ሕዝብም ብሔራዊ ሉዓላዊነታቸውን እና የግዛት አንድነታቸውን ላለማስደፈር አስፈላጊውን እርምጃዎች ሁሉ እንደሚወስዱም ነው ያስጠነቀቁት፡፡

አፈጉባኤዋ ጉብኝት ከማድረጋቸውም በፊት ቻይና በቀጣናው ያልተለመደ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓንም በመጠቆም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት፥ የያዝነውን ዓመት ጨምሮ ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሁሉ በርካታ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እና የምክር ቤት አባላት ታይዋንን ሲጎበኙ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አፈጉባዔዋ ታይዋንን ለመጎብኘት ከወሰኑ ቻይና በተለየ መልኩ ጉዳዩን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የምትመራበት ምክንያት የለም ብለዋል፤ ለሚከተለው ቀውስ እራሷ ቻይና ተጠያቂ እንደምትሆንም ነው ያስጠነቀቁት።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ በበኩላቸው ÷ ቻይና የአፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲን ጉብኝት ሰበብ አድርጋ በታይዋንና አካባቢው ፀብ-ጫሪ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር መሞከሯ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

የአሜሪካው ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ናንሲ ፔሎሲ ትናንት ሲንጋፖር መግባታቸውን ዘግቦ በመርሐ ግብራቸው መሠረትም ታይዋንን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.