Fana: At a Speed of Life!

ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በፀጥታ፣ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ አለች

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በፀጥታ፣ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲፈቱ እገዛዋን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገለፀች።
የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በየዓመቱ የአፍሪካ ሀገራትን ይጎበኛሉ።
በያዝነው ወርም የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፥ በኤርትራ፣ ኬንያ እና ኮሞሮስ ጉብኝት አድርገዋል።
ዋንግ ዪ በጉብኝታቸው ቻይና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያላትን አመለካከት አስታውቀዋል።
በቀጣናው ሠላማዊ ልማት እንዲረጋገጥም ያላቸውን ሃሳብ ማስረዳታቸውን ነው በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ያመለከተው።
ዋንግ ዪ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በአካባቢው የሚስተዋሉ ግጭቶች ከተወገዱ ትልቅ የመልማት አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
የቀጣናው ህዝቦችም የሚስተዋለውን ግጭት እንደማይፈልጉትና በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።
ቻይና በምስራቅ አፍሪካ ሠላም እና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ነው ዋንግ ዪ የተናገሩት፡፡
ቻይና የቀጣናው ሀገራት የፀጥታ፣ የልማት እና አስተዳደር ተግዳሮቶች እና ጥያቄዎች በሠላም እንዲፈቱ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗንም ነው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ቀጣናዊ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታትም በአካባቢው ሀገራት መካከል ውይይቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ዪ አሳስበዋል።
አክለውም በዚህ ጊዜ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንድነትን ማጠናከር እና መበልጸግን መሻት አለባቸው እንጂ በጂኦግራፊያዊ ድንበር ራሳቸውን አጥረው መራራቅ የለባቸውም ነው ያሉት።
ቻይና፥ ሀገራቱ የሠላም ኮንፈረንስ እንዲያዘጋጁ እና በቀጣናው ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መክረው ፖለቲካዊ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ትፈልጋለችም ነው ያሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
እንደ አዲስ አበባ – ጅቡቲ እና የሞምባሳ – ናይሮቢ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ዓይነቶች ወደ ሌሎችም የቀንዱ ሀገራት መስፋፈት አለበት ያሉት ሚኒስትሩ፥ በተለይም የቀይ ባህርና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ የባህር ዳርቻዎች በቀጣይ ለምተው ብዙ የስራ እድልና እድገትን ማምጣት ይግባል ብለዋል።
በስተመጨረሻም የቀንዱ ሀገራት ያሉባቸው የአስተዳደር ማነቆዎች ሊፈቱ የሚገባው እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ነው በማለትም ከዚህ አኳያ ቤጂንግ ልምዷን ለማካፈል እንደምትፈልግ አመልክተዋል።
አንድነቱ የተጠበቀ፣ የተረጋጋና በልማት የተሳሰረ የአፍሪካ ቀንድ እውን እንዲሆንም የብሄር፣ የሀይማኖት እና ሌሎች አካባቢያዊ ግጭቶች በአፍሪካዊ መፍትሄ ሊፈቱ ይገባል ብላ እንደምታምንም ነው የተጠቀሰው።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.