Fana: At a Speed of Life!

ቻይና የፔሎሲን የታይዋን ጉብኝት ተከትሎ በደሴቷ ላይ ተከታታይና የተመረጡ ወታደራዊ እርምጃዎችን እወስዳለሁ አለች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የፔሎሲን የታይዋን ጉብኝት ተከትሎ በደሴቷ ላይ ተከታታይና የተመረጡ ወታደራዊ እርምጃዎችን እንደምትወስድ አስታወቀች።

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ የቻይናን ተደጋጋሚ እና ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ወደጎን በመተው ማምሻውን አወዛጋቢውን የታይዋን ጉብኝታቸውን ጀምረዋል።

የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ለአፈ ጉባዔ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት በሰጠው ምላሽ፥ በታይዋን አቅራቢያ ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የቻይና ባለስልጣናት “እጅግ የከፋ አደገኛ” ያሉትን የአፈጉባዔ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ተግባራዊ መሆን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፥ የቻይና ሕዝብ ነፃነት ሠራዊት በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ ከዛሬ ጀምሮ በታይዋን ሰርጥ ተከታታይ የሆኑና የተመረጡ ወታደራዊ እርምጃዎች ይወሰዳል ብሏል።

የሠራዊቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ዉ ኩያን ለቻይና መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፥ ወታደራዊ እርምጃው የአገሪቱን ብሄራዊ ክብር፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር፣ የውጭ ጣልቃገብነትን ለመመከት፥ የታይዋንን ነፃነት ከገንጣዮች ለመከላከል በቆራጥነት የሚወሰድ እርምጃ እንደሆነም ነው ያስታወቁት።

የሠራዊቱ የምሥራቅ ዕዝ የምድር፣ የባህር ሃይልና የአየር ምድቦች በወደቧ ሰሜናዊ፣ ደቡብ ምዕራብና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚያካሂዱም ነው ቃል አቀባዩ ያብራሩት።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በአፈጉባኤዋ ጉብኝት ላይ በሰጡት አስተያየት፥ የያዝነውን ዓመት ጨምሮ ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሁሉ በርካታ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እና የምክር ቤት አባላት ታይዋንን ሲጎበኙ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አፈጉባዔዋ ታይዋንን ለመጎብኘት ከወሰኑ ቻይና በተለየ መልኩ ጉዳዩን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የምትመራበት ምክንያት የለም ብለዋል፤ ለሚከተለው ቀውስ እራሷ ቻይና ተጠያቂ እንደምትሆንም ነው ያስጠነቀቁት።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ በበኩላቸው ÷ ቻይና የአፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲን ጉብኝት ሰበብ አድርጋ በታይዋንና አካባቢው ፀብ-ጫሪ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር መሞከሯ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው፥ በታይዋን ጉዳይ ላይ “በእሳት የሚጫወቱት” የአሜሪካ ፖለቲከኞች “መጨረሻቸው አያምርም” ማለታቸውን ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

በሌለ በኩል የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ደግሞ የአፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ቤጂንግ ላይ ጫና ለመፍጠር የታለመ “ ነገር ፍለጋ ነው” ብለውታል።

ዛካሮቫ በሰጡት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው “ ሩስያ የቻይናን ‘የአንድ ቻይና’ መርህ ትደግፋለች፤ በየትኛውም መልኩ የታይዋንን መገንጠል ትቃወማለች” ነው ያሉት።

በአፈ ጉባዔዋ የታይዋን ጉብኝት ላይ አሜሪካውያኑ ባለስልጣናት አንድ ዓይነት አቋም የላቸው ነው ተንታኞች የሚሉት።

ፕሬዚዳንት ባይዳን ራሳቸው ጉብኝቱ “ጥሩ ሀሳብ አይደለም” የሚል አስተያየት አስቀድመው ሰጥተው እንደነበርም ነው እየተነገረ ያለው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.