Fana: At a Speed of Life!

ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ያጋጠሙንን ፈተናዎች እንሻገራለን- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሲከበር ዕለቱ የአንድ ቀን መታሰቢያ ከመሆን አልፎ የብሔር ብሄረሰቦች ሕገ መንግስታዊ መብቶች ይበልጥ በሚረጋገጡበትና በልዩነት ውስጥ የተፈጠረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እሴቶችን በሚያጎለብቱ ተግባራት መከበሩን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
 
ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ፥ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ያጋጠሙንን ፈተናዎች እንሻገራለን ብሏል።
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን አንኳን ለ16ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሰላም አደረሳቸሁ!!

የዘንድሮዉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞኪራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመቻቻልና የፍቅር ተምሳሌት በሆነችዉ በድሬ ዳዋ ከተማ ህዳር 29/2014 ዓ.ም ይከበራል፡፡ ዕለቱ “ወንድማማችነት ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን ዕለቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተብሎ መከበር የጀመረዉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት የፀደቀበት ቀን ምክንያት በማድረግ ነው ፡፡ ከለዉጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ዕለቱ በተለያዩ ሕዝባዊ ክንዋኔዎች ሲከበር የቆየ ቢሆንም በዋናነት ልዩነቶችን በማጉላት ላይ ያተኮረና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የሚቆጠር ሚና አልተጫወታም፡፡ በመሆኑም የለዉጡ ጉዞ ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት የሚረጋገጠዉ ዕለቱን አስቦ ከመዋል ባሻገር በሕገ-መንግስቱ ዉስጥ የተደነገጉ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ድንጋጌዎችና መርሆች እንዲከበሩ በማድረግ ጭምር መሆኑ ታምኖበት ትርጉም ያለዉ የለዉጥ እርምጃዎች ተወስዷል፡፡ የግልና የቡድን መብት ይበልጥ እንዲጠበቁ ተደርጓል፡፡ እዉነተኛ ህብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት እንዲገነባ ተሰርቷል ልዩነታችን የስጋትና መከፋፈል መንስኤ ሳይሆን የጥንካሬያችን ምንጭና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ማጌጫ ሆኖ እንዲያገለግል መሰረት በመጣል ላይ እንገኛለን፡፡

ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረዉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲከበርም ዕለቱ የአንድ ቀን መታሰቢያ ከመሆን አልፎ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ይበልጥ በሚረጋገጡበትና በልዩነት ዉስጥ የተፈጠረ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እሴቶችን በሚያጎለብቱ ተግባራት ተከብሯል፡፡

የዘንድሮዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበርን ከወትሮዉ ልዩ የሚያደረገዉ ለ27 ዓመታት በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስም እየማለ ነገር ግን በተግባር አንዱን ብሔር ከሌላዉ ብሔር ጋር እያጋጨ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትቀጥል ሲሰራ የነበረዉና በጦርነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪዉ የህወሃት ቡድን በብሔሮች አንድነት ወገቡ በተሰበረበት ማግስት መሆኑ ነዉ፡፡ አሸባሪዉ ቡድን ኢትዮጵያን ይበታትናል ብሎ የቀበረውን ፈንጂ በመተማመን ጦርነት ቢከፍትም አሸባሪዉ ቡድን ባልጠበቀ ሁኔታ የፈረሰ የመሰለዉ ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ይበልጥ ተጠናክሮ ወጥቷል፡፡ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ሲጎለብት አሸናፊነታችንም እሙን የመሆኑ ጉዳይ በታሪካችን የነበረ ብቻ ሳይሆን ዛሬም እተመሰከረ ያለ ሀቅ ሆኗል። በመሆኑም ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ያጋጠሙንን ፈተናዎች እንሻገራለን፡፡

 

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.