Fana: At a Speed of Life!

ነፃ የንግድ ቀጣናውን በታቀደለት ጊዜ እውን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ መሠረተ ልማቶች መኖራቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ነፃ የንግድ ቀጣናውን በታቀደለት ጊዜ እውን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ መሠረተ ልማቶች መኖራቸው ተገለፀ፡፡
የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክና የድሬዳዋ ደረቅ ወደብን በማቀናጀት የሚመሠረተውን ነፃ የንግድ ቀጠና አስመልክቶ በሕግ ማዕቀፎችና በመሰረተ ልማት ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስን ጨምሮ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፣ የብሔራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት አባላትና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ነፃ የንግድ ቀጣናውን በታቀደለት ጊዜ እውን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ መሠረተ ልማቶች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡
በድሬዳዋ የሚቋቋመውን ነፃ የንግድ ቀጠና እውን ለማድረግ የሚየስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በተመለከተ÷በፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች ዙሪያ የጥናት ቡድኑ የተመለከታቸውን ዝርዝር ጉዳዮች የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ጽህፈትቤት አስተባባሪ አቶ እውነቱ ታዬ አቅርበዋል፡፡
ነፃ የንግድ ቀጣናው÷ ዕቃዎች የሚራገፉበት፣ የሚስተናገዱበት ወይም የሚገጣጠሙበት እና ወደ ውጪ እንደገና የሚላኩበት ወይም ለኢንዱስትሪ ፓርክ በግብዓትነት እንዲቀርቡ የሚደረግበት ነፃ የንግድ ፓርክና የኤክስፖርት ማቀነባበሪያ ዞን መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በውይይቱ÷ የተሟላ የድንበር ተሻጋሪ እና የሀገር ውስጥ ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ያለው እና ግንኙነት የተፈጠረለት ቀጣና መሆኑ፣ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ለሚገቡ አልሚዎች እና ውስጥ ለሚገቡ ባለሀብቶች ስለሚያገኙት የቀረጥና ግብር ማበረታቻዎችም ገልፃ ተደርጓል፡፡
የኤሌክትሪክ፣ የስልክ እና ውሃ አገልግሎቶች እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማቶች መኖራቸውን እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችሉ ሁኔታዎች መኖራቸው መመላከቱን ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው÷ ነፃ የንግድ ቀጠናውን በመመስረት ሂደት አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸው÷በቀጣይ የማስፋፊያ ቦታዎችን በማመቻቸትና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ለንግድ ቀጠናው መስፋፋት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡
ወደ ነፃ የንግድ ቀጠናው የሚገቡ አልሚዎችና ባለሃብቶችን ለማበረታታት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በተደረገው ውይይት መሰረት÷ በቀጣይ ቀጠናውን ወደ ስራ ለማስገባት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.