Fana: At a Speed of Life!

ኔቶ ዓለምን በተፅዕኖው ስር ለመክተት የሚያደርገውን መሰፋፋት በንቃት መከታተል እንደሚገባ የኢራኑ ፕሬዚዳንት አስገነዘቡ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 16፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ኔቶ/ ዓለምን በተፅዕኖው ስር ለመክተት የሚያደርገውን መስፋፋት በንቃት መከታተል እንደሚገባ የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ አስገነዘቡ።

ፕሬዚዳንቱ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስርጌ ላቭሮቭ ጋር በወቅታዊ የሀገራቱ ጉዳዮች ዙሪያ እና በኑክሌር ስምምነት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ራይሲ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በተለያዩ የአለም ክፍሎች ያለውን ተፅእኖ ለማስፋት የሚደረገውን ሙከራ ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ይህ የአሜሪካ እና የኔቶ ተስፋፊነት እየተካሄደ ላለው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“ለዩክሬን ግጭት መቀስቀስ የኔቶ መስፋፋት መንስኤ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፤ ስለሆነም የምዕራቡን አለም ጨምሮ በየትኛውም የአለም ክፍል የሚደረገውን የኔቶ መስፋፋት በንቃት ማየት ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በተለይም ድርጅቱ በእስያ፣ ካውካሰስ እና ማእከላዊ እስያ ለመስፋፋት የሚያርገውን ሙከራ በንቃት መከታተል እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል፡፡

የዩክሬን ግጭትን በተቻለ ፍጥነት ማቆም አስፈላጊ መሆኑን  የገለፁት ፕሬዚዳንት ራይሲ ኢራን ግጭቱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ  እንዲያገኝ የራሷን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ስለመሆኗም አስረድተዋል፡፡

ቴህራን እና ሞስኮ  ከፍተኛ የነዳጅ እና የጋዝ ክምችት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ፥ ነገር ግን በተጣለባቸው ማዕቀብ ምክንያት ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅርብ አለመቻላቸው ተመላክቷል፡፡

የፕሬዚዳንቱ እና የሰርጌይ ላቭሮቭ ንግግሮች ኢራን እና ሩሲያ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ፍሬያማ እና ስልታዊ ትብብር ለማድረገ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ፕሬስ ቴቪ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.