Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ለጀርመን ፓርላማ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ሰጡ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በጀርመን ፓርላማ የኢኮኖሚና ልማት ትብብር ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በበይነ መረብ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ወቅት በትግራይ ክልል ስለተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ እና ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከ32 ለሚበልጡ የፓርላማ አባላት ገለጻ አድርገዋል፡፡

በትግራይ ክልል ለ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ዕርዳታ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ በመንግስት መሸፈኑንና የህወሓት ቡድን መወገዱ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የጎላ ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ ወሳኝ የሆነውን የሃይል ፍላጎቷን ለማሟላት እየሰራች ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ያነሱት አምባሳደሯ፥ ከታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ጋር ያለውን ልዩነት በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚደረገው ድርድር ለችግሩ የተሻለ አማራጭ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ ችግሩ ቀደም ሲል በተቀመጡ የመፍትሔ አማራጮች በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን አውስተዋል፡፡

በቀጣይ የሚካሄደው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሃገር ውስጥና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች መጋበዛቸውን ገልጸዋል፡፡

የጀርመን መንግስትና የፓርላማ አባላት በሰብአዊ ዕርዳታ፣ በኮቪድ19፣ በምርጫና እየተካሄዱ ባሉ የለውጥ ሥራዎች በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው የሁለቱ ሃገራት የረጅም ጊዜ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ከትካቼንኮ ቬስቨሎድ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር አለማየሁ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ፣ ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ አስመልክተው ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

በተመሳሳይ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ መቀመጫቸውን ኒውዮርክ ላደረጉ የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ በማብራሪያቸው በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ አምባሳደሮቹ ለኢትዮጵያ ላሳዩት አጋርነትና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተያያዘም በአልጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በአልጀሪያ ከቱርክ አምባሳደር መሂኑር ኦዝደሚር ጎክታስ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅት በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን፥ አምባሳደር ነብያትም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር እና በኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩም ጋብዘዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.