Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአውሮፓ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ሃይል ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአውሮፓ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ሃይል አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸው አምባሳደር ሬድዋን አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እና ዓለም  አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሀገራችን ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እና የሀሰት መረጃዎች ስርጭትን ለመመከት በዳያስፖራው የተደረገው እንቅስቃሴ ዕውቅና የሚሰጠው እና ሊመሰገን የሚገባው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
ወቅታዊና ትክክለኛ የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ የመንግሰት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መመቋቋሙንም አምባሳደር ሬድዋን ጠቅሰዋል።
 
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ እና በየሀገራቱ ከሚገኙ ሚሲዮኖቻችን ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።
 
መንግስት በቅርቡ የወሰዳቸው እርምጃዎች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ከላቸውን ፋይዳ አኳያ የሚታዩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
 
በሌላ በኩል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ላለመግባት የወሰነ ቢሆንም እንደ አንድ ልዑላዊ ሀገር ቡድኑ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመከታተል ተገቢ እርምጃ እንደሚወስድ አብራርተዋል፡፡
 
የግብረ ሃይሉ አባላትም የተደረገላቸው ገለጻ በቂ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ጠቅሰው÷በአባሎቻቸው ዘንድም ተመሳሳይ አረዳድ እንዲኖር የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በአፋር ክልል በነበራቸው ጉብኝት በህወሓት ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና የተጎዱ ነዋሪዎችን ለመደገፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለተደረገው ሀገራዊ ጥሪ የሰጡትን አመርቂ ምላሽ በሀገራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችም ተሳትፏቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከመንግስት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
 
ዲፌንዲ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያን ላይ የሚደርሰውን ያልተገባ ጫና እና የሀሰት መረጃዎችን የመመከት ዓላማን በማንገብ የተቋቋመ ሲሆን÷ በ12 የአውሮፓ ሀገራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.