Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ተወካይ ጂያን ዣኦን ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
አምባሳደር ብርቱካን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማስመለስ፣ በመጠለያ ውስጥ በማገዝ እና ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ባለው ጥረት ላደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አመስግነዋል።
 
 
መንግሥት በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እያደረገ ካለው ጥረት ጉን ለጎን በአፍሪካ እና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በችግር ውስጥ የሚገኙ ከ12 ሺህ በላይ ዜጎችን ለመመለስ ዕቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
 
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅትም እስካሁን እያደረገ እንዳለው ድጋፍ ሁሉ ለዚህ ተግባርም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ጠይቀዋል።
 
ጂያን ዣኦ በበኩላቸው÷ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ስደተኞችን ከማስመለስ እና ከማቋቋም ባለፈ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችንም በመደገፍ የራሱን የጤና ባለሙያዎች በመመደብ እና በመጠለያዎች የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎችን ተገቢውን ምክር በመስጠት ዘርፈ ብዙ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በቀጣይ የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።
 
አምባሳደር ብርቱካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ የስራ ክፍሎች ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
 
በቀጣይም በተለያዩ አገራት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በማስመለሱ ሂደት የሚደረገውን ትብብር ለማጠናከር ከመግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.