Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት  ሪክ ማቻር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሪክ ማቻር ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ነቢል የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በጸና መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር ከዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት በተጨማሪ ሀገራቱን በመንገድና በኃይል መሠረተ-ልማቶች ማስተሳሰር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደሩ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ሁኔታ እንዲሁም በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር በበኩላቸው ደቡብ ሱዳን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ያላት መሆኑን በማንሳት ይህን አቅም ለመጠቀም የመሠረተ-ልማት ትስስር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል ጸጋና የደቡብ ሱዳንን ሰፊ የነዳጅ ሃብት አቅም ማስተሳሰር አስፈላጊ መሆኑን መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ባሻገር በትግራይ ያለው ሁኔታ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተስተካክሎ በኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ ላይ ለሚነሳው ውዝግብ ቴክኒካዊ መፍትሄ እንዳለውና ጉዳዩን ፖለቲካዊ ከማድረግ ይልቅ አማራጭ መፍትሄዎች መሻት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ ያልተጠበቀና አሳዛኝ መሆኑን በማንሳት ችግሩ በውይይት ብቻ መፍታት የሚገባው መሆኑን አሳስበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.