Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር አብዱልፈታህ በኩዌት ከዲፕሎማቲክ ኮር ዲን አምባሳደር አብዶላሃድ ምቤኪ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በኩዌት የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ በኩዌት የሴኔጋል አምባሳደር እና በኩዌት የዲፕሎማቲክ ኮር ዲን አምባሳደር አብዶላሃድ ምቤኪ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያካሄደው ዘመቻ በሃገሪቱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ብቻ ሳይሆን እንደ ሃገር ህልውናን የማስቀጠል ጉዳይ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ጥቅሙ የተነካበት የህወሓት የጥፋት ኃይል በሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ላለፉት ሁለት ዓመታት የሄደበትን የጸብ አጫሪነት ተግባር መንግሥት በሆደ ሰፊነት ሲታገስ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

አምባሳደሩ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ፣ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጻረሩ የተለያዩ ተግባራትን በመፈጸምና ህገወጥ ምርጫ በማድረግ ሃገሪቱን ለመበታተን ሲሰራ መቆየቱንም አስረድተዋል።

ጥቅምት 24 ቀን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በማድረስ የሰራዊቱን ንብረት የጦር መሳሪያ በመዝረፍ የመጨረሻውን ቀይ መስመር መጣሱን የገለፁት አምባሳደሩ፤ በዚህ ምክንያት መንግሥት ህግን የማስከበር ዘመቻ እንዲያካሂድ መገደዱን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዘመቻው ዋና ሥራ መጠናቀቁን በመጥቀስም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ወንጀለኞች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ቀሪዎችን የማደን ሥራው የቀጠለ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችንና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የማቋቋምና የመገንባት ተግባራት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

አሁን ላይም መንግሥት ከዓለም ዓቀፍ በጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ በመገኘት ከመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ተቋርጠው የነበሩ በረራዎችን ጨምሮ የስልክ፣ የመብራትና ሎሎች አገልግሎቶች በክልሉ በተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች ተጀምረዋልም ነው ያለኩት በማብራሪያቸው።

አምባሳደር አብዶላሃድ ምቤኪ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው መንግሥት የሃገርን ሰላም እና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑንና በክልሉ ይህንኑ ለማስከበር የወሰደው እርምጃ ተገቢ መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.