Fana: At a Speed of Life!

አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሻሻል እንደቻሉ በአማራ ክልል የሚገኙ አርሶአደሮች ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሻሻል እንደቻሉ በአማራ ክልል የሚገኙ አርሶአደሮች ገለጹ፡፡

በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በአዊና በሌሎች በአሲዳማ አፈር ጉዳት በደረሰባቸው ቦታዎች ኖራን በመጠቀም የተሻለ ምርታማነት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ መሬታቸው በአሲዳማነት ችግር በመጠቃቱ በርካታ አመታት ምርት የሚባል ነገር እንዳላገኙ በመግለጽ መሬታቸውም ጦም አዳሪ ሆኖ ቤተሰባቸውም ተቸግሮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ካለፉት አራት አመታት ጀምሮ ኖራን በመጠቀማቸው ስንዴ፣ ጤፍና ገብስ ማምረት መቻላቸውንም ጠቅሰው፥ አሁን ላይ በሄክታር የሚያገኙት የምርት መጠን መጨመሩንም ያስረዳሉ፡፡

በክልሉም ኖራን በመጠቀም ረገድ ከግንዛቤ እጥረት በተጨማሪ የማጓጓዣና የአቅርቦት ችግር እንዳለ አንዳንድ አርሶአደሮች ገልጸዋል፡፡

አቶ አለባቸው አሊጋዝ በአማራ ክልል የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ÷ በክልሉ ከአንድ ሚሊየን ሄክታር በላይ በአሲዳማ አፈር የተጠቃ መሬት እንደሚገኝ ገልጸው ይህንንም ችግር ለመቅረፍ መንግስት ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአርሶአደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት በማከናወን፣ የኖራ ወፍጮዎችን በመትከል፣ አርሶአደሩ የኖራ ግዢ ለማከናወን የብድር አገልግሎት እንዲያገኝ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እንዲሁም በሰርቶ ማሳያዎች አማካኝነት የኖራ አቅርቦትና ተጠቃሚነት በክልሉ ባልተዳረሰባቸው ቦታዎች በስፋት ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግ አቶ አለባቸው መግለጻቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.