Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሃት የደረሰበትን መራር  ሽንፈት በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳው  ሊሸፍነው አልቻለም- የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  አሸባሪው ህወሃት የደረሰበትን መራር  ሽንፈት በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳው  ሊሸፍነው አልቻለም፤ አይችልምም  ሲል የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር ለገሰ ቱሉ በመግለጫቸው፥ “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያሸነፉበት እንቅስቃሴ ተደርጓል ነው ያሉት።

በዘመቻው ኢትዮጵያውያን በአንድ የቆሙበት እና የላቀ የአመራር ጥበብና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ታይቶ ጠላት ብትንትኑ የወጣበትም ነው ያሉት።

የአፋር ክልል፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ሸዋና ሌሎች አካባቢዎች በዘመቻው ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣታቸው፣ በደቡብ ወሎ ደሴና ኮምቦልቻን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች፥ በሰሜን ወሎም ላሊበላን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች  ነፃ መውጣታቸውን ገልጸው ሌሎች አካባቢዎችም በቅርቡ ነፃ ይወጣሉ ብለዋል።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን የደረሰበትን ሽንፈት በተለመደ ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳው  አልጋረደውም ሲሉም አክለዋል።

አሸባሪው ህወሃት የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ እርስ በዕርስ መከፋፈል መፈጠሩን ህዝባዊ ተቃውሞም ተነስቶበታል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ።

አሸባሪ ቡድኑ በርካታ አረመኔያዊ ተግባራትን መፈፀሙን ተናግረው ነገ በሚከበረው የሰብዓዊ መብት ቀን ያደረሳቸው  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  ይታሰባል ብለዋል።

ነፃ በወጡ አካባቢዎች መሰረተ ልማቶችንና መንግስታዊ አስተዳደር መዋቅሩን የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

መልሶ ግንባታው በመንግስት አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ህብረተሰቡ፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቋል።

የህወሃት ተላላኪ  ሸኔ ላይ በተወሰደ እርምጃም ሽብር ቡድኑን በማዳከም የኦሮሚያን ሰላም ማረጋገጥ እንደተቻለ ነው ያነሱት በመግለጫቸው።

ሸኔን አግዝፎ ለማሳየት የተለያዩ ዘመቻዎች ሲደረጉ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፥ ቡድኑ ግን እዚህ ግባ የማይባል እየተሹለከለከ ጉዳት የሚያደርስ የመንደር ሽፍታ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ጦርነቱ ያላለቀ በመሆኑ  የህብረተሰቡ መነሳሳትና አካባቢውን መጠበቁ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አኩሪ ተጋድሎ በርካታ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት የተቻለ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፥  በተገኙ ድሎች መዘናጋት እንደማይገባ አመልክተዋል።

አሸባሪው ህወሃት ከፍተኛ ምትና ሽንፈት የደረሰበት  የጥፋት ሀይሉ፥ በመበተኑ በየደረሰበት አካባቢ ጥቃት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት።

መጪዎቹ የበዓላት ወቅትን በመሆናቸው ይህን ከለላ በማድረግ ጠላት ጥቃት እንዳያስከትል አካባቢን በንቃት መጠበቅ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

ጦርነቱ ያስከተለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የወጣው ህግ ብዥታ ፈጥሯል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ህጉ ግን ተመላላሽ ነጋዴዎችን እንጂ ዲያስፖራውን አይመለከትም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በአሸባሪው ህወሃት የተፈጸሙ  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ለመሰነድ የሀገር ውስጥና ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን መሰማራታቸውን እና ሁኔታውን የሚያጠና ግብረሀይል መቋቋሙንም  ገልፀዋል።

ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም ወንጀሉን ገብተው እንዲመረምሩ መንግስት ጥሪ ያቀርባል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ፅህፈት ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ከሀገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ውይይት  ማድረጋቸውን ገልፀው እነዚህ ውይይቶች የኢትዮጵያና የአፍሪካን ጉዳዮች ያነሱ ናቸው ብለዋል።

 

በአፈወርቅ እያዩ እና ፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.